አምባሳደር ሬድዋን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን የበለጠ ለመሳብ መንግሥት በትኩረት እየሠራ መሆኑን ገለጹ

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

መጋቢት 9/2014 (ዋልታ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን የበለጠ ለመሳብ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ተናገሩ።

አምባሳደር ሬድዋን በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ እየተሳተፉ ከሚገኙ እና ለመሳተፍ ፍላጎት ካላቸው የህንድ ባለሀብቶች እና ከህንድ የኢንቨስትመንት ፎረም አባላት ጋር ተወያይተዋል፡፡

አምባሳደር ሬድዋን በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያ ለውጭ ባለ ሀብቶች ክፍት ያልነበሩ የኢንቨስትመንት ዘርፎችን ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ክፍት ማድረጓን ተናግረዋል፡፡

የሕንድ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ወቅትም መዋለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ሌሎች ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ መልካም አብነት መሆናቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊ ህንዳውያን ባለሀብቶች የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት፣ ከፀጥታ እና ከቀረጥ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን ከባለሀብቶቹ ለተነሱት ጥያቄዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት እንደ አገር ለሁሉም ባለሀብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚሰራ አምባሳደር ሬድዋን አረጋግጠዋል፡፡

ህንዳውያን ባለሀብቶች በበኩላቸው ኢትዮጵያ በዘርፉ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በፍጥነት መፍታት ከቻለች በአፍሪካ ቀንድ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ አኅጉር ትልቋ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መዳረሻ የመሆን አቅም አላት ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከባለሀብቶች የሚነሱ ጥያቄዎችን በማዳመጥ እልባት ለመስጠት ቁርጠኛ መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡