ችግር ላይ የወደቁ ዜጎችን የመደገፍ ሥራ

መስከረም 5/2014 (ዋልታ) በአማራና አፋር ክልሎች ልዩ ትኩረት የሚሹ ቦታዎች ላሉ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ዙሪያ እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ግምገማ ተደርጓል፡፡
በዚህም በባህር ዳር እና ሰመራ ከተሞች የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከላት ተከፍተው ከ10 ክላስተሮች የተውጣጡ ተጨማሪ የባለሙያ ቡድኖች ወደ ቦታው መላካቸወ ተገልጿል፡፡
ከፊል ሰሜን ወሎ እና ዋግኸምራ ላይ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ዕለታዊ የሰብዓዊ እርዳታ ሥርጭት ተጀምሯል ነው የተባለው፡፡
በመጠለያዎች የሚገኙ ዜጎችን ከመደገፍ ጎን ለጎን ቤት ለቤት ችግር ላይ የወደቁ ዜጎችን ለመድረስ የተጀመረው ሥራም ተጠናክሮ ይቀጥላል ተብሏል።
ቀደም ሲል ከተሰማራው 20 ተንቀሳቃሽ የሐኪሞች ቡድን በተጨማሪ ሌላ የህክምና ቡድኖች ለማሰማራት ከተለያዩ ክልሎች ጋር በመተባበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል በአንዳንድ የአፋር፣ ሰሜን ወሎ እና ደቡባዊ ትግራይ አካባቢዎች የበረሃ አንበጣ ክስተት እየታየ በመሆኑ ሳይባባስ ለመከላከል ተጨማሪ የግብርና ባለሙያዎች እና ግብዓት ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ወደስፍራው ለማድረስ ዝግጅት መጠናቀቁ ነው የተገለጸው፡፡
በተለያዩ ዘርፎች የተሰራው የመጀመሪያ ደረጃ የጉዳት ዳሰሳ ጥናት እንዳመላከተው፣ ትምህርት ቤቶችንና የጤና ተቋማትን ጨምሮ በርካታ የመሰረተ ልማት አገልግሎቶች ተጎድተዋል፡፡
ከዕለት ደራሽ እርዳታ ጎን ለጎን የመሰረተ ልማት መልሶ ግንባታና ማቋቋም ተግባራት ለማስጀመር ዝርዝር ጥናት የሚያደርግ ከመንግስት ተቋማትና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት የተውጣጣ የሙያተኞች ቡድን ሥራውን የሚጀምርበት የስራ መመሪያ መሰጠቱን ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡