አሸባሪው የሕወሓት ወራሪ ቡድን የኅልውናችን ስጋት በመሆኑ ሁልጊዜም በተጠንቀቅ ተዘጋጅተን መጠበቅ አለብን – ርዕሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)

ርዕሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)

ታኅሣሥ 27/2014 (ዋልታ) አሸባሪው የሕወሓት ወራሪ ቡድን የኅልውናችን ስጋት በመሆኑ ሁልጊዜም በተጠንቀቅ ተዘጋጅተን መጠበቅ አለብን ሲሉ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ገለጹ።

ርእሰ መሥተዳድሩ ባስተላለፉት መልዕክት ኅልውናችንን ለማስከበር መላ ሕዝባችን ያለምንም ልዩነት በአንድነት የከፈለው መስዋእትነት የጠላትን ወረራ መቀልበስ እንዳስቻለ ኹሉ በቀጣይም ለኅልውናችን ስጋት የሆነውን ወራሪ ቡድን ለመዋጋት ብቻ ሳይሆን ለውስጣችን ሰላምና ልማትም ወሳኝ በመሆኑ አንድነታችን አጠናክረን ማስቀጠል ይገባናል ብለዋል።

በጦርነቱ የተዳከመውን የከተሞቻችን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በመጪው ጊዚያት የቱሪስት ከተማዎችን የበለጠ እንዲነቃቁ የሚከበሩ በዓላትን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ለመሻሻል መስራት እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳደሩ አስታውቀዋል፡፡

ከመደበኛ አከባበሩ በተጨማሪ ዲያስፖራው ከሀገር ፍቅር ስሜት በመነጨ እያደረገ ላለው ጉብኝትና ድጋፍ ከበዓሉ ጋር ተዳምሮ የተለየ ቀለምና ድምቀት እንዳለው ማስተጋባቱም ለውስጥም ለውጭም ዘርፈ ብዙ መልእክት እንዳለው መረዳት እንደሚገባ መናገራቸውን  አሚኮ ዘግቧል።

በአንድ በኩል ኅልውናችን ለማስከበር፣ በሌላ በኩል የውስጥ ሰላማችንና ልማታችንን ለማፋጠን ኹላችንም እኩል ትኩረት ሰጥተን መንቀሳቀስ ይገባናልም ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።