አብሮነታችንን ለማደፍረስ የሚሠሩ አካላትን በአንድነት በመመከት ሕብረታችንን ማጠናከር ይገባል – የሃይማኖት አባቶች

መስከረም 15/2016 (አዲስ ዋልታ) በተለያዩ መንገዶች አብሮነታችንን ለማደፍረስ የሚሠሩ አካላትን በአንድነት በመመከት ሕብረታችንን ማጠናከር ይገባል ሲሉ የሃይማኖት አባቶች አሳሰቡ፡፡

ከሁሉም ቤተ እምነቶች የተወጣጡ የሃይማኖት አባቶች በአንዋር መስጂድ በመገኘት የፅዳት ዘመቻ መርኃ ግብር አከናውነዋል።

1ሺሕ 498ኛው የነብዩ መሀመድ መውሊድ በዓል “የይቅርታው ነብይ” በሚል መሪ ቃል በታላቁ አንዋር መስጂድ በነገው ዕለት በድምቀት ይከበራል።

በዚህም የሃይማኖት አባቶች፣ የመዲናዋ ነዋሪዎች እና የሙስሊሙ ማህበረሰብ በጋራ በመሆን ታላቁ የአንዋር መስጂድን አፅድተዋል።

በጽዳት መርኃ ግብሩ በዓላት የጋራ አብሮነታችንን የምናጠናክርባቸው እና እሴቶቻችንን የምንገልጽባቸው በመሆናቸው የሀገር ግንባታና መልካም ገፅታን በማጎልበት ረገድ ትልቅ ሚና አላቸው ሲሉ የሃይማኖት አባቶች ገልፀዋል።

የመውሊድ በዓል በታላቁ አንዋር መስጂድ ሃይማኖታዊ ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ ከሀምሳ ዓመታት በላይ መከበሩ ይታወቃል።

በፈቲያ ሁሰን