አትሌት ትዕግስት አሰፋ በበርሊን ማራቶን የዓለም ክብረወሰን በማሻሻል አሸነፈች

አትሌት ትዕግስት አሰፋ

መስከረም 13/2016 (አዲስ ዋልታ) ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትዕግስት አሰፋ በበርሊን ማራቶን የዓለም ክብረወሰን በማሻሻል አሸነፈች፡፡

በዓለም አትሌቲክስ የፕላቲንየም ደረጃ ያለው 49ኛው የጀርመን በርሊን ማራቶን ዛሬ ሲደረግ በሴቶች ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትዕግስት አሰፋ በአስደናቂ ብቃት አሸንፋለች።

አትሌቷ ርቀቱን ለመጨረስ 2:11:53 ጊዜ የፈጀባት ሲሆን ከዚህ ቀደም ክብረወሰኑ በኬንያዊቷ አትሌት ብሪጅድ ኮስጌይ 2:14:04 በሆነ ሰዓት ተይዞ ነበር።

በበርሊን ማራቶን የዓለም ክብረወሰን በማሻሻል ያሸነፈችው አትሌቷ ባለፈው ዓመትም የበርሊን ማራቶንን ማሸነፏ ይታወሳል፡፡

በወንዶች ኬንያዊው ኢሉድ ኪፕቾጌ ርቀቱን በበላይነት አጠናቅቋል፡፡

በሐብታሙ ገደቤ