ኢትዮጵያና ኮይካ የ16 ሚሊዮን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ


መጋቢት 12/2016 (አዲስ ዋልታ) ኢትዮጵያ እና የኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ኮይካ) የ16 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰውና የኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶንጉ ኪም የተፈራረሙ ሲሆን ድጋፉ በኢትዮጵያ የኤክስፖርት ምርቶችን ጥራት ለማስጠበቅ እና የህጻናትን መቀንጨር ለመከላከል የሚደረጉ ጥረቶችን ለማገዝ ነው ተብሏል።

ኮይካ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረጉ በኢትዮጵያ የግብርና ምርት ጥራትና ደረጃን ማሻሻል ላይ የሚሰሩ ስራዎችን እንደሚደግፍም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።

በተጨማሪም በግብርና ምርት ማሻሻል ላይ የሚሰራው ፕሮጀክት 10 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የተመደበለት መሆኑ ተጠቁሟል።

በተለይም ሀገሪቱ ወደ ውጭ ከሚላክ የግብርና ምርት የምታገኘውን ገቢ በመጨመር ዘርፉ በሀገሪቱ አጠቃላይ ምርት ላይ ያለውን ድርሻ ይበልጥ ለማሳደግ እንደሆነም ተገልጿል።

የህጻናት መቀንጨርን ለመከላከል የሚሰራው ፕሮጀክት ስድስት ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የተመደበለትና ከአምስት ዓመት እድሜ በታች ለሚገኙ ህጻናት፣ ለነፍሰ ጡር ሴቶችና ለሚያጠቡ እናቶች እንዲሁም ለልጆቻቸው የተመጣጠነና ጥራቱ የተጠበቀ ምግብ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ ተመልክቷል፡፡