በክልሉ ከበጋ መስኖ ከ18 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተሰበሰበ


መጋቢት 13/2016 (አዲስ ዋልታ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በዘንድሮ የበጋ መስኖ ለምርት ከደረሰው 80 ሺሕ 474 ሄክታር መሬት ከ18 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡ ተገለጸ።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትልና የእርሻ ልማት ዘርፍ ኃላፊ መላኩ ባፋ ከአዲስ ዋልታ ዲጂታል ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ በመደበኛ መስኖ 117 ሺሕ 494 ሄክታር በተለያዩ አትክልቶች በመሸፈን 28 ሚሊዮን 294 ሺሕ 892 ኩንታል ምርት ለማምረት መታቀዱን ተናግረዋል።

በዚህም እስካሁን ከ106 ሺሕ ሄክታር መሬት በላይ የተለያዩ አትክልቶችን ማልማት መቻሉን የጠቀሱት ኃላፊው ለምርት ከደረሰው 80 ሺሕ 474 ሄክታር መሬት 18 ሚሊዮን 398 ሺሕ 410 ኩንታል ምርት መሰብሰብ መቻሉን አመልክተዋል።

የውሃ አማራጮችን በመጠቀም በዓመት ሁለትና ሦስት ጊዜ በማምረት አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ጠቁመው በቲማቲም፣ ሽንኩርት እና ጥቅል ጎመን እንዲሁም በፍራፍሬ ላይ ትኩረት ተደርጎ በመሠራቱ ውጤት መታየቱንም ገልጸዋል፡፡

በተያያዘ በበጋ መስኖ ስንዴ 11 ሺሕ 230 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ 2 ሺሕ 600 ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን ምርት መሰብሰብ መጀመሩንም ተናግረዋል።

ለአርሶ አደሮች የተለያዩ ግብዓቶችን በማቅረብና የግብርና ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ በማድረግ ተከታታይ ድጋፎች እየተሰጠ ነው ያሉት ምክትል ኃላፊው የበጋ መስኖ ልማት ስራ መጀመሩ አርሶ አደሩ መሬቱን፣ ጊዜውን እና ጉልበቱን በአግባቡ እንዲጠቀምና ምርቱን እንዲያስድግ እድል መፍጠሩን ጠቁመዋል፡፡

በመስኖ ልማት የተጀመረው ሥራ ምርትን በመጨመር የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ጉልህ ሚና እየተጫወተ መምጣቱንም ገልጸው አርሶ አደሩ ያመረተውን ምርት ለገቢያ እንዲያቀርብ የገበያ ትሥሥር የመፍጠር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በተያያዘ ወጣቱ የውሃን አማራጭ ተጠቅመው በግብርናው መስክ እንዲሰማሩ እየተደረገ መሆኑንና በተቀናጀ የግብርና ሥራ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

የመስኖ ልማት የአርሶ አደሩን የማምረት አቅም እንዲጨምርና የውሃ አማራጮችን የመጠቀም ባህሉ እንዲጎለብት በማድረጉ በአርሶ አደሩ ኑሮ መሻሻልና በኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ አይነተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በሠራዊት ሸሎ