የካቲት 24/2013 (ዋልታ) – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሳምንታዊ የሀገሪቱን ምጣኔ ሃብታዊ፣ ፖለቲካዊ እና የፐብሊክ ዲፕሎማቲክ ሥራዎች በሚመለከት ለብዙኃን መገናኛ ተቋማት መግለጫ ሰጥቷል፡፡
መግለጫውን የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሳምንቱ በሀገሪቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ፋይዳ ያላቸው ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል፡፡ በተለያዩ ሀገራት ኢትዮጵያን በመወከል የሚሰሩ ዘጠኝ አምበሳደሮች በፕሬዝዳንቷ እና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሥራ መመሪያ ተሰጥቷቸው ተሸኝተዋል ብለዋል፡፡
አምባሳደሮቹ በተመደቡባቸው ሀገራት ሥራ እንደሚጀምሩም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል በሳምንቱ ውስጥ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከኖርዌይ አቻቸው ጋር በስልክ ባካሄዱት ውይይት አቶ ደመቀ በትግራይ ክልል ስለተካሄደው ሕግ የማስከበር እርምጃ፣ ትግራይን መልሶ ስለማቋቋም እና የሰብዓዊ ድጋፍ አገልግሎት በሚመለከት ማብራሪያ ሰጥተዋቸዋል፡፡
አልጀዚራን እና ቢቢሲን ጨምሮ ሌሎች የውጭ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት እና የሰብዓዊ ድርጅቶች ጉዳዩን በሚመለከት ለዘገባ እንዲገቡ መፈቀዱንም አውስተዋል፡፡
በሰሞኑ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት መግለጫ እና በግብጽና ሱዳን የህዳሴው ግድብ ግንባታ ድርድር አቋም ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት አምበሳደር ዲና ኢትዮጵያ በውስጣዊ ጉዳዮቿ የማንንም ሀገር ጣልቃ ገብነት እንደማታስተናግድ ግልጽ አቋሟን አራምዳለች ነው ያሉት፡፡
የግብፅ እና ሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሁለትዮሽ ስምምነትን በሚመለከትም ኢትዮጵያ በብሔራዊ ጥቅሟ ላይ ያላት አቋም ወጥ በመሆኑ የተለየ ነገር እንደማይኖር ነው የገለፁት፡፡ የሦስቱን ሀገራት ድርድር ደቡብ አፍሪካ ስትመራው መቆየቷን ያወሱት አምባሳደር ዲና በቀጣይ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ታስቀጥለዋለች ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
በቴል አቪቭ፣ ጃካርታ እና አንካራ ምጣኔ ሃብታዊ ፋይዳ ያላቸው ኤግዚቪሽኖች መካሄዳቸውን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት 1 ሺህ 200 ኢትዮጵያዊን ወደሀገራቸው መመለሳቸውንም አምባሳደሩ በመግለጫቸው አመላክተዋል፡፡
የኢትዮ- ኤርትራ ግንኙነት አሁን ሰላማዊ ነው፤ በቀጣይም ዘላቂ የንግድ እና ቀጣናዊ ግንኙነት ለመመስረት እየተሠራ ነውም ብለዋል፡፡
የአብመድ ዘገባ እንዳመለከተው ከኢትዮ – ሱዳን የድንበር ጉዳይ ጋር በተያያዘም የኢትዮጵያ አቋም ጦርነት ለሁለቱም ሀገራት አይጠቅምም የሚል ነው፤ ነገር ግን የበዛ ትዕግስት ማሳየታችንን እንዲረዱት እናደርጋለን ብለዋል ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው፡፡