ሚያዝያ 30/2015 (ዋልታ) ኢትዮጵያ እና ማልታ በአቪዬሽን፣ በቱሪዝምና በዲፕሎማሲ ዘርፎች ስልጠና ለማድረግ የሚያስችላቸውን የትብብር ሰነድ በዛሬው ዕለት ተፈራረሙ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የማልታ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ እና የንግድ ሚኒስትር የሆኑትን ኢያን ቦርግን ዛሬ በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡
በሁለትዮሽ፣በቀጣናዊ እና በአለማቀፍ መድረክ ያላቸውን ትብብር እና ወዳጅነት ላቅ ወዳለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ መወያየታቸው ነው የተገለጸው።
ከውይይታቸው በኋላ የጋራ መግለጫ የሰጡ ሲሆን ማልታ ባለፉት ሁለት ዓመታት ለኢትዮጵያ ያደረገችውን ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ እና ባለፈው ዓመት ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ በመክፈት ላሳየችው አጋርነት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ እና ውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ምስጋና ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የማልታ የውጭ ጉዳይ እና ንግድ ሚኒስትር ኢያን ቦርግ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቁልፍ ሚና ያላት አገር መሆኗንና ለዚህም የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክለውም ማልታ የተመ.ድ ፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል በመሆኗ በቆይታዋም የኢትዮጵያን እና የአፍሪካን ጥቅም ያስከበረ ስራ እንደምትሰራ አረጋግጠዋል ።
ሚኒስትሩ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ትግበራ አወንታዊ መሆኑን ጠቅሰው የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።
ሁለቱ አገራት መካከል በተፈረመው ስምምነት መሰረት ማልታ በተለይም በአቪዬሽን ፣ በትምህርትና ዲፕሎማቲክ ስልጠና ዘርፎች ያላትን የተሻለ ተሞክሮ ለማጋራት ምቹ አጋጣሚ የፈጠረ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።