ሰኔ 30/2013(ዋልታ) – “የዲጂታል ትብብር የኮቪድ-19 ተፅዕኖን ለመቋቋምና ከጉዳቱ በዘላቂነት ለማገገም” በሚል ዓለም አቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ህብረት ያዘጋጀው የበይነ መረብ መድረክ ተካሂዷል።
መድረኩ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ተቋቁሞ ለማገገምና ለመጠናከር ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስለሚጫወተው ሚና ለህበረተሰቡ ግንዛቤ ለማስጨበጥና ትርጉም ያለው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ለውጥ ለማምጣት የተዘጋጀ ነው።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሐመድ (ፒኤችዲ) በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የተጎዳውን የዓለም ኢኮኖሚ ለመጠገን የዲጂታል ትብብር እና ጠንካራ የበይነ መረብ ግንኙነት ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በዲጂታል ትብብር መስክ ከዓለም ባንክ፣ ከአውሮፓ ህብረት፣ ከኢስቶኒያ እንዲሁም ከሌሎች ሀገራት እና ድርጅቶች ጋርም በትብብት እየሰራች ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ እየሰራቻቸው ያሉ የማሻሻያ ስራዎች በበይነ-መረብ ግንኙነት ችግር ተፈትነዋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ይህንን ለመቅረፍ የማሻሻያ ስራዎች እየተሰሩ ስለመሆናቸው ጠቁመዋል።
የዩኒሴፍ ምክትል ስራ አስፈፃሚ ፋያዝ ኪንግ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም ላይ 1.6 ቢሊየን ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳደረገና ይህንን ችግር ለመቅረፍ ትምህርት ቤቶችን ከበይነ መረብ ጋር በማገናኘት ዲጂታል ትምህርት መስጠት ላይ ሲሰራ መቆየቱን ገልፀዋል።
በመድረኩ የተባበሩት መንግስታትና የልዩ ልዩ ሀገራት ከፍተኛ ኃላፊዎች የተሳተፉ ሲሆን የኮቪዲ-19 ወረርሽኝ ያሳደረው ተፅዕኖና ከተፅዕኖው ለመውጣት የተወሰዱ እርምጃዎች ላይ ውይይት ማድረጋቸውን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።