ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከተማሪዎች ጋር በመሆን በጉለሌ እፅዋት ማዕከል ችግኞችን ተከሉ

ሰኔ 30/2013 (ዋልታ) – የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከተማሪዎች ጋር በመሆን በጉለሌ እፅዋት ማዕከል ችግኞችን ተክለዋል።

“የሀገር ተረካቢነታችንን በአረንጓዴ አሻራችን ኢትዮጵያንችንን እናልብስ” በሚል ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ከ30 ሺህ በላይ ተማሪዎች፣ መምህራን እና የትምህርት ማኅበረሰብ አመራሮች ችግኞችን ተክለዋል።

“ተማሪ እያለን ሰኔ 30 ዓመቱን ሙሉ የተማርነውን ውጤት ለማወቅ በጉጉት የምንጠብቅበት ቀን ነው” ያሉት ምክትል ከንቲባዋ፣ ዛሬ ደግሞ ተማሪዎች ኢትዮጵያን እናልብሳት በማለት ችግኝ በመትከል አሻራ ማኖራቸውን ገልጸዋል።

ዛሬ የተተከሉ ችግኞችም ለነገይቱ ኢትዮጵያ እና ለአዲስ አበባ ልምላሜ የተላበሰች፣ ለኑሮ የተመቸች እንድትሆን የሚያደርግ በመሆኑ ተማሪዎች ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን መኮትኮት እና መንከባከብ ይገባል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በዛሬው ዕለት በከተማዋ በሁሉም የመንግሥት እና የግል ትምህርት ቤቶች በአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር የችግኝ ተከላ መርኃግብር ከ100 ሺህ በላይ ችግኞች እንደሚተከሉ የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ መግለጻቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።