ኢዜማ የምርጫውን ውጤት በይሁንታ እንደሚቀበል ገለጸ

                ኢዜማ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ
ሰኔ 17/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የድምፅ መስጠት ሂደት መጠናቀቁን ተከትሎ መግለጫ ሰጥቷል::
የዴሞክራሲ መሰረትን ለመትከል የጅማሮ መንገድ በሆነው 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ መራጮች የተሳተፉበትን መንገድ የሚበረታታ ነው የምርጫ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ኢዜማ ውጤቱን በይሁንታ እንደሚቀበል የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ገልፀዋል::
ይሁንና ፓርቲው በተወዳደረባቸው አካባቢዎች ከ400 በላይ ግድፈቶችን የታዘበ መሆኑና ይህን እክልም ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁን ገልፆ፣ ቦርዱም ትክክለኛነትን ያማከለ ውሳኔን ማሳለፍ ይጠበቅበታልም ብሏል::
የምርጫ ውጤቱ በምርጫ ቦርድ ይፋ ሳይደረግ ፓርቲው ምንም አይነት ድምዳሜ እንደማይሰጥ እንዲሁም ዜጎችም ከመላምት መቆጠብ እንዳለባቸው ፓርቲው መግለጫው አስታውቋል::
(በሄብሮን ዋልታው)