እንደሻው ጣሰው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ ፕሬዝዳንት ሆነው ተሾሙ

አዲስ የተመሰረተው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ ፕሬዝዳንት ሆነው የተሸሙት እንደሻው ጣሰው

ነሐሴ 13/2015 (አዲስ ዋልታ) እንደሻው ጣሰው ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሚል በአዲስ በተመሰረተው ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት ማዕረግ የክልሉ ፕሬዝዳንት ሆነው ተሾሙ።

እንደሻው ላለፉት 30 ዓመታት በተመደቡበት የስራ ኃላፊነት ሁሉ ሀገራቸውን በቅንነትና በታማኝነት ሲያገለግሉ የቆዩና በማገልገል ላይ የሚገኙ መሆናቸው ተነስቷል።

ለአብነትም በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር አካዳሚክ ክፍል በተለያዩ የስራ ኃላፊነቶች፣ በኢፌዲሪ ፖሊስ ኮሚሽን በፌደራል ኮሚሽነርነት እንዲሁም በብሄራዊ የመረጃ ደህንነት ረዳት ኮሚሽነርነትና በሌሎችም በተመደቡባቸው የስራ ኃላፊነት ያበረከቱት አስተዋፅኦ ለሹመት እንዳበቃቸው ተነግሯል።

በዚህም የእንደሻው ሹመት በሙሉ ድምፅ የፀደቀ ሲሆን የተሰጣቸውን ኃላፊነት በቅንነትና በታማኝነት ለመወጣት ቃለ መሀላ ፈፅመዋል።

የቀድሞ የክልሉ ፕሬዝዳንት ርስቱ ይርዳው ለአዲሱ ተሿሚ እንደሻው ጣሰው የህገ መንግስት ርክክብ አድርገዋል።

በትዕግስት ዘላለ