ግንቦት 10/2014 (ዋልታ) መንግሥት የዋጋ ግሽበቱን ለማረጋጋት በወሰደው እርምጃ ከሸቀጦች ታክስ ይገኝ የነበረ ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ እንዳይሰበሰብ መደረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት ያለፉት ዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ወቅት እንደተገለጸው መንግሥት የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት የምግብ ሸቀጦች ያለውጪ ምንዛሪ (በፍራንኮ ቫሉታ) እንዲገቡ አድርጓል፡፡
በዚህም መንግሥት በምግብ ሸቀጦች ላይ ጥሎት የነበረውን ታክስና ቀረጥ በማንሳቱ ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ሳይሰበሰብ እንዲቀር መደረጉን ሚኒስቴሩ ያስታወቀው፡፡
የስንዴ ዋጋን ለማረጋገት በተደረገውም ጥረትም ባለፉት ዘጠኝ ወራት 320ሺሕ ቶን ስንዴ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ የተደረገ ሲሆን የምግብ ዘይትን በተመለከተም ገበያውን ለማረጋጋት የምግብ ዘይት ግዢ ውል መፈጸሙም ተገልጿል፡፡
የፌዴራል መንግሥት የበጀት ጉድለትን ለማጥበብና የሀገር ወስጥ ብድር እንዳይጨምር ለማድረግ በወሰደው እርምጃም ከመደበኛ በጀት የ5 ቢሊዮን ብር የወጪ ቅነሳ የተደረገ ሲሆን 26 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ አዳዲስ የካፒታል ፕሮጀክቶች ወደሚቀጥለው በጀት ዓመት እንዲዛወሩ መደረጋቸው ከሪፖረቱ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የውጭ ሀብት ለማሰባሰብ በተደረገውም ጥረትም ባለፉት ዘጠኝ ወራት 2 ቢሊዮን ዶላር በብድርና በዕርዳታ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲፈስ ታቅዶ በዚሁ ወቅት 2 ነጥብ 26 ቢሊዮን ዶላር ወደ ሀገር ውስጥ የፈሰሰ ሲሆን አፈጻጸሙም 111 ነጥብ 1 በመቶ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የእዳ ክፍያን በተመለከተም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለውጭ ብድር 24 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ለመክፈል ታቅዶ 20 ነጥብ 7 ቢሊዮብ ብር ክፍያ እንደተፈጸመና አፈጻጸሙም 83 በመቶ መሆኑ ታውቋል፡፡
የሀገር ወስጥ እዳ ክፍያ በተመለከተም 10 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የሀገር ውስጥ ብድርን ለመክፈል ታቅዶ 17 ቢሊዮን ብር እዳ ክፍያ የተፈጸመ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የገንዘብ ሚንስትር አህመድ ሽዴ በሥራ በአፈፃፀም ሪፖርቱ ላይ በሰጡት አስተያየት በሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማት በዕቅዱ መሰረት ያልተከናወኑ ተግባራትን በመለየት በቀሪው ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
በግምገማው ላይ ከገንዘብ ሚኒስቴር በተጨማሪ ለሚኒስቴሩ ተጠሪ የሆኑት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር፣ የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ፣ የመንግሥት ግዢ ባለስልጣን እንዲሁም የመንግሥት ግዢ አገልግሎት የዘጠኝ ወራት አፈፃፀማቸው ቀርቦ ግምገማና ውይይት መደረጉን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡