ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ጠንካራ ግንኙነት ይኖረናል – የተለያዩ አገራት ከፍተኛ ኃላፊዎች

መስከረም 25/2014 (ዋልታ) “ከአዲሱ የኢትዮጵያ መንግስት ጋር ጠንካራ ግንኙነት ይኖረናል” ሲሉ የተለያዩ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ኃላፊዎች ገለጹ።

የተለያዩ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ሃላፊዎች፤ የመንግስት መስረታ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ለሚኖራት ግንኙነት አዲስ ምእራፍ የሚከፍት መሆኑን ገልጸዋል።

የጅቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሃመድ አሊ የሱፍ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነት በቁርጠኝነት የሰራች አገር ናት ያሉ ሲሆን ኢትዮጵያ አሁን ላይ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እያለፈች መሆኑን ጠቅሰው ሆኖም “ኢትዮጵያውያን ችግራቸውን በራሳቸው አቅም መፍታት የሚችሉ ጠንካራ ህዝቦች መሆናቸውን ሁሉም ሊገነዘብ ይገባል” ብለዋል።

ጀቡቲ ሁሌም ከኢትዮጵያውያን ጎን የምትቆም ጠንካራ አቋም ያላት አገር መሆኗንም ነው ያብራሩት።

ጅቡቲ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ወዳጅነት ከሌሎች ሀገራት ጋር ካላት ግንኙነት ይለያል የሚሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ ሁለቱ ሀገሮች በመሰረተ ልማት ጭምር የተሳሰረ ጥብቅ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የተመሰረተው አዲስ መንግስት የሁለቱ አገራት ግንኙነትን ወደ አዲስ አድማስ እንደሚያሸጋግረው ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።

የኡጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ጆን ሙሊምባ፣ ኡጋንዳና ኢትዮጵያ በምንም አይነት ሁኔታ የማይቀየር አጋርነት እንዳላቸው ጠቁመዋል።

ሁለቱ አገሮች የአፍሪካ ቀንድን ወደ አንድ ለማምጣትና በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በጋራ እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፣ በቀጣይም ይህንኑ ተግባር አጠናክረው አንደሚቀጥሉ አውስተዋል።

ኢዜአ እንደዘገበው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያን ለመምራት ድጋሚ እድል ስለተሰጣቸው መደሰታቸውንም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ በሆነ አዲስ መንግስት መመስረታቸው የሚደነቅ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ ናቸው።

እስራኤል በዴሞክራሲ በጽኑ የምታምን ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፣ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ በዴሞክራሲያ ሂደት መንግስት መቋቋሟ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በጎ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።