ከወጪ ንግድ ከ3 ነጥብ 6 ቢሊዮን በላይ ዶላር ገቢ መገኘቱ ተገለጸ


ነሐሴ 15/2015 (አዲስ ዋልታ) በ2015 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ ከ3 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር በላይ ማግኘት መቻሉን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ 2015 በጀት ዓመት የወጪ ንግድ አፈፃፀም እና የ2016 በጀት ዓመት ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ ውይይት ከሀገር ውስጥ ላኪዎች ጋር እያካሄደ ይገኛል።

በዚህም በ2015 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ ከ3 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር በላይ ማግኘት መቻሉን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል።

የወጪ ምርት በጥራት፣ በመጠንና በአይነት በማሳደግ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ፍላጎት ለማሳካት ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር መመካከር አስፈላጊ መሆኑም ተገልጿል።

በመድረኩ በዘርፉ ህገወጥነትና ኮንትሮባንድ፣ የፋይናንስ አቅርቦት ችግር፣ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የገበያ ዋጋ ያልተመጣጠነ መሆንን የመሰሉ ተግዳሮቶች ከውጪ የሚገኘውን ምንዛሬ እንዲቀንስ አድርጎታልም ነው የተባለው።

የወጪ ንግዱን ለማሳደግና ችግሮችን ለመፍታት በርካታ ስራዎች መከናወናቸውም ተመላክቷል።

በተለይም ሚኒስቴሩ የኤክስፖርት ልማትና ፕሮሞሽን እስትራቴጂ ሰነድ በማዘጋጀት እየሰራ መሆኑንም አስታውቋል።

በተጨማሪም ለዘርፉ ማነቆ የሆነውን የኮንትሮባንድ ንግድ ለመከላከል ከጉምሩክና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑ ተነስቷል።

በብሩክታይት አፈሩ