ከ558 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ነሐሴ 15/2015 (አዲስ ዋልታ) የጉምሩክ ኮሚሽን ከነሐሴ 5 እስከ 11/2015 ዓ.ም ባደረገው ክትትል 558 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በኩል መያዙን አስታወቀ፡፡

ከተያዙት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ውስጥ 523 ነጥብ 1 ሚሊዮን ግምት ያላቸው የገቢ የኮንትሮባንድ እቃዎች ሲሆኑ 35 ሚሊዮን ብር የሚገመት ዋጋ ያላቸው ዕቃዎች ደግሞ የወጪ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድኃኒት፣ ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ የጦር መሳሪያዎች፣ ጫት፣ ልዩ ልዩ አደንዛዥ እጾች፣ የምግብ ዘይት እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል ተብሏል፡፡

በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር የላቀ አፈጻጸም የተመዘገበ ሲሆን በዚህም አዲስ አበባ ኤርፖርት፣ ድሬዳዋ እና ጅግጅጋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት ሲሆን በቅደም ተከተላቸው 273 ሚሊዮን፣ 113 ሚሊዮን እና 44 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዝ መቻላቸው ተጠቁሟል፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በበረራና በጥቆማ የተያዙ ሲሆን እቃዎቹን ሲያዘዋዉሩ የተገኙ 12 ግለሰቦች እና 10 ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ የኮሚሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡