መስከረም 3/2015 (ዋልታ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ በሙስና የተመዘበረ ገንዘብ ማሳገድ መቻሉን ፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የፍትህ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አወል ሱልጣን ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተለይም ሙስናን ከመከላከል አንፃር የተከናወኑ ተግባራትና የተገኙ ውጤቶችን አብራርተዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሙስና የተመዘበረ ገንዘብ፣ መሬት፣ ቤትና ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ ሌሎችን ሀብቶችን ተከታትሎ ማስመለስ መቻሉን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በክርክር ላይ ያሉና ክስ የተመሰረተባቸው የመንግስትና የሕዝብ ሃብቶች እንዲታገዱ መደረጉን ተናግረዋል።
በዚህም 701 ሚሊዮን ብር ጥሬ ገንዘብ፣ ከ744 ሚሊዮን ብር በላይ የሼር ገንዘብና የ27 ሚሊዮን ብር ቦንድም እንዳይንቀሳቀስ በፍርድ ቤት መታገዱን አስረድተዋል።
በተጨማሪም 41 ሺሕ ካሬ ሜትር በላይ መሬት ታግዶ በፍርድ ቤት የክርክር ሂደት ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የሙስና ወንጀሎች ውስብስብና ጊዜ የሚወስዱ ክርክሮችን የሚፈልጉ መሆናቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ በፍርድ ቤት እየተካሔደ ያለው ክርክር እስኪጠናቀቅ የተመዘበረ ሃብት እንዳይንቀሳቀስ መደረጉን ጠቁመዋል።
በሙስና ተመዝብረዋል ተብለው የተያዙ 364 ተሽከርካሪዎች፣ 155 ቤቶችና 617 የተለያዩ ማሽነሪዎችም በተመሳሳይ ለሦስተኛ ወገን ተላልፈው እንዳይሰጡና እንዳይሸጡ መደረጉንም አስታውቀዋል።
የታገዱ ሃብቶች ላይ እየተደረገ ያለው ክርክር እስኪጠናቀቅ ጉዳትና ብልሽት እንዳይደርስባቸው አስፈላጊው ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።
ከ88 ሚሊዮን ብር በላይ፣ 10 ሺሕ ካሬ ሜትር መሬትን ጨምሮ የተለያዩ ተሽከርካሪዎችንና መኖሪያ ቤቶች ለመንግስት ገቢ መደረጉን ገልጸዋል።
በሙስና የተመዘበሩ ሐብቶች ላይ የሚደረገው የፍርድ ቤት ክርክር ሲጠናቀቅ መንግስትና ሕዝብ ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኙ ይደረጋልም ብለዋል።