በኦሮሚያ ክልል ከመጪው ሰኞ ጀምሮ በሁሉም ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ስራ እንደሚጀመር ተገለጸ

መስከረም 3/2015 (ዋልታ) በኦሮሚያ ክልል ከመጪው ሰኞ ጀምሮ በሁሉም የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ስራ እንደሚጀምር የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ።

በኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ የትምህርት ቤቶች ማሻሻያ ፕሮግራም ዳይሬክተር ወርቅነህ ነጋሳ እንደገለጹት በክልሉ ትምህርት መጀመር የሚያስችል ዝግጅት ተጠናቋል።

የመምህራን ዝግጅት፣ የመማሪያ መጻሕፍት ማዘጋጀትና የትምህርት ቤቶች ዝግጅት ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።

የተማሪዎች ምዝገባ ከነሐሴ 23 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው ይኸው ስራ እስከ መስከረም 8 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

በዚሁ የትምህርት ዘመን በክልሉ 11 ነጥብ 3 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁን የገለጹት ዳይሬክተሩ በእስከ አሁኑ ሂደት የተማሪዎች ምዝገባ ከ95 በመቶ በላይ መጠናቀቁን አመልክተዋል።

በዝግጅት ምዕራፉ 34 ሺሕ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች የተገነቡ ሲሆን በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መሰረት የተማሪዎች መማሪያ መጻሕፍት በ’ሶፍት ኮፒ’ ለሁሉም ትምህርት ቤቶች መድረሳቸውን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የመምህራን ተማሪዎች ጥምርታ የማስጠበቅ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ነው የጠቀሱት።

ከመጪው መስከረም 9 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ ሁሉም የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ስራ ይጀመራል ብለዋል።

የተጠናቀቀው ክረምትን ጨምሮ በተለያዩ አካላት ተሳትፎ 6 ሺሕ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ መሆኑን ገልጸው 5 ሺሕ የሚሆኑት አፈፃፀማቸው ከ90 በመቶ በላይ መጠናቀቃቸውን አመልክተዋል።

የ2015 ዓ.ም የመማር ማስተማር ሂደት በሁሉም የክልሉ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚሰጠው በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መሆኑን የገለጹት ደግሞ በቢሮው የሥርዓታ ትምህርት ትግበራ ዳይሬክተር ደረጀ ታደሰ ናቸው።

በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት እርከኖች ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል እና ከ7ኛ እና 8ኛ ክፍል ተብለው በሁለት እርከን መከፈላቸውን ተናግረዋል።

ትምህርቱ ከአስተማሪ ተኮር ይልቅ ተማሪ ተኮር የሆነ የመማር ማስተማር ሂደት ተግባራዊ የሚደረግበት መሆኑን ጠቅሰው በዚህም አስተማሪዎች ሁኔታዎችን ማመቻቸትና የተሳለጠ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲተገበር ማስቻል እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

አመች ሁኔታዎች የመፍጠር ስራና መምህራን በአስተሳሳብ፣ በአመለካከት፣ በክህሎትና በአቅም ግንባታ የማዘጋጀት ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

በክልሉ ከ16 ሺሕ የሚጠጉ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ መረጃን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።