ጳጉሜን 2/2015 (አዲስ ዋልታ) ክልላችን አሁን ወደ ደረሰበት ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ ለሰሩ የመከላከያ ሰራዊት፣ ለክልል ጸጥታ ኃይሎችና ለመላው የክልሉ ህዝብ ታላቅ ክብር አለን ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ተናገሩ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በአማራ ክልል የተቀናጀ የሰላም ማስከበር ስራ ተግባራዊ በመሆኑ በአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች ሰላም ማስፈን መቻሉንም ገልፀዋል።
ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ”የመስዋዕትነት ቀንን” አስመልክቶ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት የመከላከያ ሰራዊት፣ የክልሉ የጸጥታ ኃይሎችና ህዝቡ ባደረገው የተቀናጀ ጥረት ክልሉ ቀድሞ ወደ ነበረበት ሰላም እየተመለሰ ነው።
የመከላከያ ሰራዊት ግዳጅን የመፈጸም ብቃትና ህዝባዊነት፣ በህዝባችን አስተዋይነት፣ የነቃ ተሳትፎና በክልሉ የጸጥታ ኃይሎች የጋራ ጥረት ተፈጥሮ የነበረውን የፀጥታ ችግር ማርገብ መቻሉን ተናግረዋል።
በተካሄደው የተቀናጀና የተደራጀ ሰላም የማስከበር እርምጃ አሁን ላይ በአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች ሰላምን ማስፈን መቻሉን አስታውቀዋል።
ክልሉን የማፍረስና ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በኃይል የመናድ እኩይ ሴራ መክሸፉንም አስገንዝበዋል።
የክልሉ ህዝብ የሚያነሳቸው የትናንትና የዛሬ ጥያቄዎቹ የሚፈቱት በሰላማዊ መንገድ በሚካሄድ ውይይትና በኢትዮጵያዊነት ማእቀፍ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም ወገኖች ከክልሉ መንግስት ጎን ተሰልፈው ለተግባራዊነቱ እንዲሰሩ አሳስበዋል።
በተጨማሪም በየደረጃው ላሉ የፖለቲካ አመራሮች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ወጣቶች በክልሉ ሰላም ለማምጣት በተደረገው ጥረት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
ቢበዛ እስከ መስከረም ወር 2016 ዓ.ም መጨረሻ መንግስታዊ አስተዳደርንና የጸጥታ መዋቅሩን እስከ ቀበሌ ድረስ እንደገና በማደራጀት በአዲስ መንፈስ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንደሚገባም ተናግረዋል።
በመልሶ ማደራጀት ትግበራ ላይ አቅም ያላቸው፣ በአመለካከታቸው የተለወጡና በስነ ምግባራቸው ምስጉን የሆኑ አመራሮችን ወደ ፊት ለማምጣት በትኩረት እየተሰራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ይህም የክልሉ ህዝብ በተለያየ ጊዜ የሚያነሳቸውና በየአካባቢው የሚፈቱ ጥያቄዎችን ኃላፊነት በመውሰድ ለመፍታት ቅድሚያ ተሰጥቶ እንደሚሰራ ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።
የመንግስት መደበኛ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና ሌሎች ተግባራትን ፈጥኖ ለማስጀመር ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተካሄደ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
የክልሉን ምርታማነት ለማሳደግ፣ ትምህርት በጊዜው ለማስጀመርና ጤናው የተጠበቀ ማህበረሰብ ለመገንባት ትኩረት እንደሚደረግ ገልፀዋል።