ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ በሀገራዊ ምክክሩ ላይ የሚሳተፉ ግለሰቦችን የመለየት ስራ ሊጀምር ነው

ነሐሴ 17/2015 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በመዲናዋ የተሳታፊ ልየታና የአጀንዳዎች አሰባሰብ ሰራ ከነገ ጀምሮ ማከናወን እንደሚጀምር አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ የተወካዮች ልየታ በሁለት ምዕራፍ እንደሚከናወንና የመጀመሪያው ለተባባሪ አካላቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና የሚሰጥ መሆኑን ገልጿል፡፡

በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ በኮሚሽኑ የተሳታፊ ልየታን በመምራት እና በማስተባበር የሂደቱን ውጤታማነት ይከታተላል ተብሏል።

ኮሚሽኑ በ119 ወረዳዎች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች የሚያስመርጥና ተመራጮች በአጀንዳ አሰባሰቡ ላይ እንዲሳተፉ የሚያደርግ ይሆናልም ነው የተባለው።

ተወካይ ያስመርጣሉ ተብለው ከተለዩት የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ መምህራን እና የማህበረሰብ መሪዎች እንደሚገኙበት ተነስቷል።

ኮሚሽኑ ሂደቱን የሚመራ ሲሆን ተባባሪ አካላት ሂደቱ አካታች፣ አሳታፊ፣ ግልጽነትና ተአማኒ እንዲሆን ይሰራል ተብሏል።

ኮሚሽኑ ምክክር ያስፈለገው ግጭት በመኖሩ መሆኑን ገልፆ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎችም የልየታ ስራው እንደሚከናወን ተገልጿል።

የመዲናዋ ነዋሪዎች ለሂደቱ መሳካት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክትና ማንኛውንም ጥያቄ በተወካዮቻቸው አማካኝነት እንዲያቀርቡ ተጠይቋል።

በብሩክታይት አፈሩ