ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታን በተመለከተ ከሀረሪ ክልል መንግስት የተሰጠ መግለጫ

እንደሚታወቀው በአማራ ክልል በታጠቁ ጽንፈኛ ቡድኖች አማካኝነት እየደረሰ የሚገኘው ጥቃት በክልሉ ሰብዓዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል።

በክልሉ የታጠቁ ጽንፈኛ ቡድኖች አማካኝነት እየተደረገ የሚገኘው እንቅስቃሴም የሀገር እና ህዝብ ደህንነት ስጋት ከመሆኑም በተጨማሪ በህገመንግስቱ እና በህገመንግስታዊ ስርዓቱ ላይ አደጋ የደቀነ መሆኑን የክልላችን መንግስት በፅኑ ያምናል።

የአማራ ክልል መንግስትና ህዝብ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በነበረው ጦርነት ከደረሰው ጉዳት ሳያገግም ለሌላ ጦርነት እና ችግር በመዳረጉ የክልላችን መንግስት ማዘኑን በዚህ አጋጣሚ ይገልጻል።

በአሁኗ ኢትዮጵያ ሁኔታ በትጥቅ ትግል የሚመለስ ጥያቄ አለመኖሩን በመገንዘብ ችግሮችን በነፍጥ ሳይሆን በሰለጠነ መንገድ በመነጋገር መፍታት አስፈላጊ መሆኑን መገንዘብ ይገባል።

የአማራ ሕዝብ መብቶችና ጥቅሞች ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጥቅሞች ጋር የተያያዙ መሆናቸውን በመገንዘብ በሰላማዊ መንገድ ከመታገል ይልቅ የሀይል አማራጭን ለጥያቄዎች መፍቻ መሳሪያ አድርጎ መንቀሳቀስ ህዝቡን ለከፍተኛ ችግር መዳረግ በመሆኑ ፍፁም ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው።

ጽንፈኛው ቡድን ከሰላም ይልቅ ነፍጥ በማንገብ የአንድነታችን አርማ የሆነውን ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት በመተንኩስ እና የሰራዊቱን ስም ማጥፋት ዘመቻ እያካሄደ ይገኛል።

በመሆኑም የክልላችን መንግስት መከላከያ ሰራዊቱን መንካት ሉአላዊነታችንን መዳፈር መሆኑን በጽኑ ያምናል።

የክልላችን ህዝብ እና መንግሥት ከአማራ ክልል ህዝብ ጋር በመሆን የአንድነታችን አርማ የሆነው ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ሌሎች የፀጥታ ሀይሎች እየዳረጉ ከሚገኙ ፅንፈኛ ቡድኖች ነፃ ለማውጣት እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ያረጋግጣል።

መላው የክልላችን ህዝብም ይህንን ሀገር አፍራሽ እንቅስቃሴ ለመግታት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሁሉ የበኩሉ እንዲወጣ በዚህ አጋጣሚ ጥሪውን ያቀርባል።

የሀረሪ ክልላዊ መንግሥት
ነሀሴ 1 ቀን 2015 ዓ.ም
ሐረር