ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ ከሶማሌ ክልላዊ መንግሥት የተሰጠ መግለጫ


የሶማሌ ክልል ህዝብና መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት በሀገራችን ህዝቦችና በብሔራዊ ሉዓላዊነታችን ላይ ያጋጠሙትን የጸጥታ መደፍረስ ችግሮች እንዲሁም በሀገር ነጻነት ላይ በውጭ ወራሪዎችና በሀገር ውስጥ ጸረ-ሰላም ኃይሎች የሚሸረቡ የጠላት ሴራዎች ከሀገር ደጀን የሆነውን ከጀግናው መከላከያ ሰራዊትና ከሌሎች ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ደሙንና አጥንቱን የከሰከሰና በብሔራዊ ጥቅማችን የማይደራደር ህዝብ መሆኑን ከማንም ያልተሰወረ ሀቅ ነው።

ይሁን እንጂ ሰሞኑን በአንዳንድ የሀገራችን ክፍሎች ላይ በጸረ-ሰላምና ፅንፈኛ ቡድኖች በተፈጠረው የጸጥታ ችግር በውይይትና በሰለጠነ መንገድ ከመፍታት ይልቅ በማይሳካ ቅዠት ሴረኞች በሸረቡት ሴራ አማካኝነት በዴሞክራሲያዊና በህዝቦች ምርጫ የመጣውን መንግሥት በአፈሙዝ በሁከት እረከባለሁ የሚሉት አካላት በተፈጠረው ችግርና የዜጎች የሰላም እጦት የሶማሊ ክልል መንግስት በጽኑ ያወግዛል።

ከዚህ በተጨማሪም የሶማሌ ክልል ህዝብና መንግሥት የሀገር ደጀን የሆነው መከላከያችን መንካት የሀገርን ሉዓላዊነት መንካት መሆኑንና በሴረኞች የሚሸርበውን እኩይ ተግባር ለአፍታ እንደማይታገስ ከወዲሁ ያሳውቃል።

የሶማሌ ክልል መንግሥት በማንኛውም ሁኔታና ማንኛውም ጊዜ ላይ የኢትዮጵያውያን አንድነት አርማ ከሆነው ከጀግናው መከላከያችን ጎን እንደሚሆን ያምናል።

በሌላ በኩል የአማራ ክልል ህዝብ መብቶችና ጥቅሞች ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጥቅም ጋር የተሳሰረና በአንድነት በመቻቻል ፤በፍቅርና በመከባበር ላይ የተመሰረተ መሆኑን የሶማሌ ክልል ህዝብ ያምናል።

በዚህም በቅርቡ በሰላም የተቋጨው የሰሜኑ ጦርነት ገና ሳናገግም፣ መርህ አልባ በሆነ አካሔድ ላይ በሚገኘው ፅንፈኛ ቡድን ፣ የአማራ ህዝብ ላይ በተሸረበ ሴራ የሰላም መደፍረስና የህይወት ዋጋ ባስከፈለ መልኩ እየሆነ ያለውን ተግባር የሶማሌ ክልላዊ መንግሥትና ህዝብ በፅኑ ያወግዛል።

በመጨረሻም ህዝቡ የሚያነሳው ጥያቄዎች በጋራ በውይይት በመነጋገርና በጠረጴዛ ላይ መፍታት እንጂ ዘመኑን የማይመጥን እሳቤን በነፍጥ የሚመለስ ጥያቄ አለመኖሩንም የክልላችን ህዝብና መንግሥት ያምናል።

የሶማሌ ክልል መንግሥት
ነሀሴ 1/2015 ዓ.ም
ጅግጅጋ