ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታን አስመልክቶ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሰጠ መግለጫ

ነሐሴ 1/2015 (አዲስ ዋልታ) ሰላም እስተንፋስ ላለው ፍጡር ሁሉ የህልውናው ማረጋገጫ ነው። ሰላም ለአፍሪካችን፣ ሰላም ለኢትዮጵያችን፣ ሰላም ለህዝባችን የማንደራደርበት የህዝባችን ህልውና ነው! ወጥቶ መግባት የምናረጋግጥበት መሠረታዊ ፍላጎት ነው!! ሰላም ለህብረተሰባችን ቅንጦት ሳይሆን እለት እለት የምንሰራበት ጉዳይ ነው!!

የኢትዮዽያ መንግስት ሰላምን የማስከበር ጉዳይ ለህዝቦቿ የልማት መረጋገጫ ዋነኛው መንገድ ነው ብሎ በፅኑ ያምናል! ለሰላም መከበር እና መረጋገጥ የሚከፈለውን ማንኛውም መስዋትነት እየከፈለ ይገኛል:: ለዚህም ቁርጠኛ አቋሙን ሁሉ በሚያደርጋቸው ውሳኔዎች አረጋግጧል::

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሰሞኑን ባጋጠመው የፀጥታ መደፍረስ እና የሰላም እጦት ምክንያት በክልሉ ህዝብ ላይ ጉዳት እየደረሰ ይገኛል። የክልሉን ጥሩ የሰላም ንፋስ በክሎ፣ ለማንኛውም ሰላማዊ የንግግር መንገዶች በሩን ዘግቶ፣ በድንፋታ ፣ በህገ ወጥነት እና በኢ-ሰብአዊነት ነፍጥ አንግቦ መንግስታዊ ስርዓቱን ለማፍረስና ስልጣን በኃይል ለመቆጣጠር በግልፅ እየተናገረ ያለው የዘራፊና ወንበዴ ስብስብ እንዲሁም ህገ -ወጥ አደረጃጀት በክልሉ ህዝብና መንግስት ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳት አድርሷል፣ በማድረስም ላይ ይገኛል።

የክልሉ መንግስት በመደበኛው የፀጥታ መዋቅሩ ይህንን ያጋጠመውን የሰላም መደፍረስ እና ህገ ወጥ አካሄድ ሊቆጣጠረው ባለመቻሉ ፤ እንዲሁም እየደረሰ ያለው ጉዳት ወደለየለት ደረጃ ከመድረሱ በፊት ለፌዴራል መንግስት በፃፈው ደብዳቤ መንግስት ህገ-መንግስቱ በሚፈቅደው ህጋዊ አሰራር መሰረት ኃይል አሰማርቶ የክልሉን ሰላም ወደ ነበረበት እንዲመለስ እና ፅንፈኛ ወንበዴዎቹ ላይም ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቋል።

በዚሁ መሰረት የፌዴራል መንግስት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በክልሉ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ያወጀ ሲሆን ዝርዝር የአዋጁ መመሪያዎችና የአዋጁ አስተግባሪ አደረጃጀቶችም ተዋቅረው ወደ ስራ ተገብቷል።

ይህ ፅንፈኛ እና የዘራፊዎች ስብስብ ከክልሉ መንግስት እና መንግስታዊ መዋቅር ቀጥሎ ዋነኛ ጠላት ብሎ የፈረጀውና ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ እያንቋሸሸና እያጥላላ የሚገኘው የኢትዮጵያ የሉዓላዊነት መገለጫ የሆነውን የአገር መከላከያ ሰራዊት ነው።
ጀግናው መከላከያ ሰራዊታች የአንድነታችን አርማ፣ የሉዓላዊነታችን መገለጫ፣ የመጨረሻው የህልውናችን ካስማ ነውና የአገር መከላከያን መንካትም ሆነ በጠላትነት መፈረጅ አገርን ማፍረስ ብሎም ህዝቦቿን በሙሉ መንካትና መፈረጅ ነው። መከላከያ ሰራዊታችን የአንድ ማንነት ስብስብ ሳይሆን ከሁሉም ኢትዮጵዮጵያዊያን ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች እናቶች አብራክ የወጣ የሀገር ሉአላዊነት ምሰሶ መሆኑን ያረጋገጠ ሠራዊት ነው!

ሰላም ወዳዱና ሰው በልቶ የሚጠግብ የማይመስለው የአማራን ህዝብ በዚህ የመኸር እና የአዝመራ ወቅት በነዚህ የጥፋት እና የዘራፊዎች ስብስብ አማካኝነት ሰላማዊ ኑሮው ታውኳል፣ መውጫ መግቢያው ተሰናክሏል፣ የንግድ እንስቃሴውም ተስተጓጉላል። ይህ ስብስብ በክልሉ የሚገኘው አርሶ አደር እንኳ ያረሰውን ማሳ በዘር እንዳይሸፍ አዝመራውን እንዳያዘምር ያደረገ ሲሆን ይህም ከፍተኛ ጉዳት ሆኖ ቀጥሏል።

የአማራ ክልል ሕዝብ እንደ ሌላው ህዝብ ሁሉ ሰላም ሆኖ መስራት እና ወጥቶ መግባት የሚገባው ሆኖ ሳለ፤ አሁን ላይ ግን በነዚህ የዘራፊዎች እና ህገ ወጦች ስብስብ ይህ ነው ተብሎ የማይገለፅ መጠነ ሰፊ ጉዳት እየደረሰበት ይገኛል። የክልሉ ህዝብ መብቶችና ጥቅሞች ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች መብትና ጥቅም ጋር በቀጥታ የተሳሰረ ነው።

የአማራ ክልል ህዝብ ጉዳት የሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጉዳት ነው። የአማራ ክልል ህዝብ ሰላም የሁሉም ክልል ህዝቦች ሰላም ነው። የትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ ሰላም ሲደፈርስ የኢትዮጵያ ሰላም ይደፈርሳል።

የዓለምም ሆነ የአሁኗ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የማያስተናግደውን መንገድ የመረጡት እነዚህ የዘራፊዎች እና ህገ ወጦች ስብስብ በትጥቅ ትግል እና በአፈሙዝ የሚመለስ ጥያቄም የሚገኝ ስልጣንም አለመኖሩን ሊገነዘቡ አልቻሉም። በአሁኗ ኢትዮጵያ ማንኛውም ጥያቄ በጠረጴዛ ዙርያ እና በውይይት መልስ የሚያገኝባት እንጂ በጠመንጃ እና በአመፅ የምታስተናግደው ጥያቄም ሆነ የምትሰጠው ምላሽም አይኖርም!

የዘራፊና ህገ ወጡ ቡድን የክልሉን እና የህዝቡን ሰላም እያወከ እና ህዝቡን እያሰቃየ ያለ ለዚሁ አላማ ታስቦ የተፈጠረ ኃይል እንጂ የአማራ ክልል ወኪልም ለአማራ ህዝብ የሚታገልም አይደለም።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የከተማችን ነዋሪዎች እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ዛሬም ከክልሉ መንግስት እና ሕዝብ ጎን በመቆም ይሄንን ሀገር አፍራሽ እና የዘራፊ ስብስብ ኢሰብአዊ ድርጊቱን በፅኑ ይቃወማል!

ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመቆም እንደ ወትሮው ሁሉ ደጀንነቱን ያረጋግጣል! የከተማውን ሰላም በማረጋገጥ የህገ-ወጦችን ተግባር በህግ ሥርአት ያስከብራል!

የአማራ ክልል እና ህዝብ ከሰሜኑ ደም አፋሳሽ ጦርነት ጉዳት ሳያገግም በስሙ ምለው በሚገዘቱ የጥፋት ኃይሎች ይህን አይነት አስከፊ ችግር ስላጋጠመው እያዘነ ፤ እንደ አስፈላጊነቱ የከተማ አስተዳደሩ በሁሉም ረገድ ከክልሉ ህዝብና መንግስት ጎን በመቆም ይህንን አጥፊ ቡድን ኢሰብአዊ ድርጊቶቹን ይቃወማል።

የዚህ የጥፋት ኃይል ከአማራ ክልል ቀጥሎ አዲስ አበባን የሽብር እና የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ በተለያየ መንገድ እየሞከረ እንደሚገኝ ተደርሶበታል። እነዚህ አጥፊ ቡድኖች እራሳቸው በጠመቁት የፀብ አጀንዳ አዲስ አበባን እና የአዲስ አበባን ህዝብ የአላማቸው ማስፈፀሚያ ለማድረግ ከተማዋን ደግሞ የግጭት እና ብጥብጥ አውድ ለማድረግ በተግባር እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።

ሆኖም ሰላም ወዳዱ እና ሚዛናዊው የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ ግዜውን፣ እውቀቱን፣ ገንዘቡን እና ጉልበቱን ለሰላም እና ልማት የሚያውል ቢሆንም፣ በህልውናው ላይ በሰላሙ ላይ እና በልማቱ ላይ የሚቃጣን ማንኛውንም አደጋ እና ስጋት እንደ ወትሮው ሁሉ በግንባር ቀደምነት ይፋለማል። ልማቱንም ያስቀጥላል !!

ይህ የጥፋት ቡድን ለዚህ እኩይ ዓላማው ማስፈፀሚያነት የሚያገለግሉና ምንም አይነት ግጭት ከሌለበት አካባቢ የግጭት ሽሽት እና ተፈናቃይ በማስመሰል በርካታ ፀጉረ-ልውጦችን አስርገው በማስገባት በከተማው ውስጥ የጥላቻ፣ የመከፋፈል እና የአመፅ አላማቸውን ለማራመድ እና የጠመቁትን ሴራ ወደ ህዝቡ ለመርጨት ሲሞክሩ በእኩይ ተግባራቸው ሲንቀሳቀስ ተይዘዋል::
ከተማ አስተዳድራችን እንደ ሁል ጊዜው ሁሉ በቁርጠኝነት ህገ ወጦችን በህግ ስርዓት ያስይዛል!

በመሆኑም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይህንን መሰል እንቅስቃሴ በንቃት እየተከታተለ ለህዝቡ ይፋ የሚያደርግ ሲሆን ህዝቡን ያሳተፈ እርምጃዎችንም ይወስዳል!

በተጨማሪም እንደ አገር የገጠመን ይህንን ችግር የጋራ ርብርብ የሚሻ በመሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የከተማችን ነዋሪዎች ከጀግናዉ የመከላከያ ስራዊታችን፤ ከአማራ ክልል መንግስት እና ህዝብ ጎን በመቆም እንደ ወትሮው ሁሉ አስፈላጊውን ቁርጠኛ ድጋፍ ያደርጋል!!

ሰላም ወዳድነቱን በሥራ እና ደጀንነቱን በቁርጠኛ ትግል ያረጋግጣል!
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር
ነሐሴ 2015 ዓ.ም
አዲስ አበባ