ዜጎች የኮቪድ-19 ምርመራን ሲያከናውኑ የቲቢ ምርመራ ማድረግ እንዳለባቸው ተገለጸ

መጋቢት 13/2013 (ዋልታ) – ዜጎች የኮቪድ-19 ምርመራን ሲያከናውኑ የቲቢ ምርመራ ማድረግ እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ የቲቢ በሽታን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሰራችው ስራ አበረታች ቢሆንም፣ የቲቢ በሽታ ይገኝባቸዋል ተብሎ ከሚታሰቡት ሰዎች ዉስጥ 29 በመቶ የሚሆኑት ወደ ህክምና ተቋማት አለመምጣታቸው በሽታው በሚፈለገው ልክ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ተግዳሮት ሆኗል ነው የተባለው፡፡

15ኛው አመታዊ የቲቢ ምርምር ጉባኤ እና በኢትዮጵያ ለ24ኛ ጊዜ የሚከበረው አለም አቀፍ የቲቢ ቀን በጤና ሚኒስቴር በአርማወር ሀሰን ምርምራ ኢኒስቲትዩት እና በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አዘጋጅነት ከመጋቢት 13 ጀምሮ ለተከታታይ ሶስት ቀናት የተለያዩ ምርምሮች የሚቀርቡበት ጉባኤ በማካሄድ እየተከበረ ነው፡፡

የአለም ጤና ድርጅት በየአመቱ ይፋ የሚያደርገው መረጃ እንደሚያመላክተው በኢትዮጵያ 175 ሺህ በላይ ዜጎች በየአመቱ በቲቢ በሽታ የሚያዙ ሲሆን፣ 21 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡

ይህም በየቀኑ 57 ሰዎች በየሰዓቱ ደግሞ 2 ሰዎች እንደሚሞቱ እንደሚያመላክትና የበሽታውን አስከፊነት የሚያሳይ ነው፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ ኢትዮጵያ ይህንን ተላላፊና አስከፊ በሽታ ለመከላከል በአምስት ዓመቱ ስትራቴጂ እቅድ በማውጣት ኅብረተሰቡን በማንቃት ስለበሽታው ግንዛቤ በመፍጠር ሰፋፊ ስራዎች እየሰራች ነው፡፡ በዚህም አመርቂ የሚባል ውጤት ማየት ተችሏል ነው ያሉት፡፡

በሽታውን ለመከላከል የተለያዩ ስራዎች ቢሰሩም በበሽታው ከሚያዙ ዜጎች ውስጥ ከመቶ 10 ሺህ ያልበለጡት ብቻ ህክምና ማግኘታቸው እንደ አንድ ችግር ሆኗል፡፡

ከዚህ ባለፈ እንደ ሀገር መድሀኒትን የተላመደ የቲቢ በሽታ መስፋፋቱ በሽታውን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር አዳጋች አድርጎታል ነው የተባለው፡፡

15ኛው አመታዊ የቲቢ ምርምር ጉባኤ በኢትዮጵያ የሚታየውን የቲቢ በሽታ በምን መልኩ መግታት ይቻላል የሚለውን ለማሳየት የሚያስችሉ የተለያዩ የቲቢ ምርምር ጥናቶች ይቀርባሉ፡፡

እነዚህ ጥናቶች በሀገር አቀፍ እና በአለም አቀፍ ደረጃ የተጠኑ ጥናቶችን በመውሰድ የቲቢ በሽታን በዘላቂነት ለመቆጣጠር የሚያስችል ግብዓትን ለመውሰድ የሚያግዙ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት በአለም አቀፍ ደረጃ የቲቢ በሽታን ለመቆጣጠር የተሰሩ ስራዎችን ዳግም ወደኋላ እየተመለሱ በመሆናቸው ዜጎች የኮቪድ-19 ምርመራን ሲያከናውኑ የቲቪ ምርመራን ማድረግ አለባቸው ተብሏል፡፡

በየአመቱ መጋቢት 15 የሚከበረው አለም አቀፍ የቲቢ ቀን በኢትዮጵያ ለ24ኛ በአለም ደግሞ ለ39 ጊዜ የቲቢ በሽታ ስርጭትን ለመቆጣጠር “ጊዜው አሁን ነው” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ይገኛል፡፡

(በስመኝ ፈለቀ)