አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት የሚኒስትሮች ስብሰባን በበይነ መረብ ተሳተፉ

መጋቢት 13/2013 (ዋልታ) – የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት “ ሴቶች ለሰላም፣ ለባህልና የሴቶች አካታችነት በአፍሪካ “ በሚል ርዕስ በሚኒስትሮች ደረጃ ባዘጋጀው ስብሰባ ተሳትፈዋል፡፡
አምባሳደር ሬድዋን በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በፌዴራል እና በክልል ደረጃ ሴቶችን በከፍተኛ የመሪነት ቦታዎች ማሳተፏን አብራርተዋል፡፡ እንዲሁም ሀገሪቱ በርካታ ሴቶችን በሰላም ማስከበር ማሰማራቷ፤ የሚያኮራት ተግባር መሆኑን ጠቅሰዋል፡
በኮቪድ-19 በሽታ ምክንያት ሴቶች ለኢኮኖሚ ጫና፣ ከትምህርት ገበታቸው እንዲርቁ፣ ያለዕድሜ ጋብቻ እንዲመሰርቱ እና ለቤት ውስጥ ጥቃቶች ተጋላጭ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸው አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በፊት በሴቶች ዙሪያ የተገኙ አበረታች ውጤቶች ወደ ኃላ እንዳይመለሱ በትኩረት መሰራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ሴቶች ለማህበረሰቡ ከሚያበረክቱት ፋይዳዎች አንጻር በተለይም ለገጠር ሴቶች የትምህርት ዕድል እንዲመቻች፤ የሴቶች ተሳትፎ በፖለቲካ እንዲያድግ ድጋፎች መደረግ እንዳለበት ጠይቀዋል፡፡
የኮሮና በሽታን በመዋጋት ሴቶች እያደረጉ ላሉት አበርክቶ ዕውቅና መስጠት አስፈላጊ መሆኑን እንዲሁም በሰላም ማስከበር ዙሪያ እያሳዩ ያሉትን አበረታች ውጤቶች ታሳቢ በማድረግ ፤ ለዩኒፎርም ለባሾቹ ተገቢ ድጋፍ ማድረግ እንደሚስፈልግ ማስገንዘቡን ከውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡