የህንድ ግዙፍ ኩባንያ በፋርማሲዩቲካል ዘርፍ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ የማምረት ፍላጎት እንዳለው ገለጸ

ነሐሴ 5/2015 (ዋልታ) ካሊክስ ኬሚካልስ እና ፋርማሲዩቲካልስ የተሰኘ የህንድ ግዙፍ ኩባንያ በፋርማሲዩቲካል ዘርፍ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ የማምረት ፍላጎት እንዳለው ገለፀ፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ የኩባንያውን ተወካዮች በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

የኩባንያው ተወካዮች በቆይታቸው ኩባንያው ስለ ኢንቨስትመንት እቅዱ ያለውን ዝርዝር ሀሳብ ለዋና ስራ አስፈፃሚው አቅርበዋል።
ዋና ስራ አስፈፃሚው የኩባንያው የኢንቨስትመንት ሀሳብ አድንቀው ኮርፖሬሽኑ ኢንቨስትመንቱ በአፋጣኝ እውን እንዲሆን ያልተቋረጠ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠው ተወካዮቹ ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክን እንዲጎበኙ ጋብዘዋል።

ኩባንያው መቀመጫውን ህንድ አድርጎ በአለም 60 በመቶ የሚሆኑ ለወባ እና ለሳንባ ነቀርሳ መድሀኒት የሚያገለግሉ ግብዓቶችን የሚያመርት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በአለም ላይ ያሉ ግዙፍ መድኃኒት አምራቾች ለምርት ሂደት የሚረዷቸውን ግብዓቶች ከዚህ ኩባንያ እየተረከቡ እንደሚገኙም መገለጹን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን መረጃ ያመለክታል፡፡