የመኪና ነጭ ጭስ የሚፈጠርባቸው ምክንያቶች!

 

የመኪና ነጭ ጭስ የሚፈጠርባቸው ምክንያቶች!

በሳሙኤል አማረ

ግንቦት 8/2015 (ዋልታ) ነጭ ጭስ በተለያዩ ችግሮች ወይም ምክንያቶች ይፈጠራል። ብዙ ጊዜ የሚከሰትበት ዋናዉ ምክንያት ግን የማቀዝቀዣ ፈሳሽ (coolant) ወደ ሲሊንደር ገብቶ ከነዳጅ እና አየር ጋር መቀላቀል እና መቀጣጠል ነዉ።

የማቀዝቀዣ ፈሳሽ ሲሊንደር ዉስጥ ገብቶ የሚቀጣጠልበት አጋጣሚ የሚፈጠርበት ምክንያት ምንድ ነዉ?

ለዚህ የማቀዝቀዣ ፍሳሽ (internal coolant leakage) ሶስት ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸዉ።

1. የሲሊንደር ሄድ ጋዝኬት መበላት

ሲሊንደር ሄድ ጋዝኬት (Cylinder head gasket) በሲሊንደር ሄድ እና በሲሊንደር ብሎክ መካከል ይገኛል። በዋናነት ሲሊንደር ዉስጥ የሚታመቀዉ ጋዝ ሊክ እንዳያደርግ እንዲሁም የማቀዝቀዣ ፈሳሽ እና ዘይት ወደ ሲሊንደር ገብቶ ከነዳጅ ጋር እንዳይቀላቀል የሚያደርግ ክፍል ነዉ።

ይህ ጋዝኬት ከተሰነጠቀ ወይም ከተበላ ኩላንት በዚህ ስንጥቅ አድርጎ ወደ ሲሊንደር ይገባል። ከዛም አብሮ በሚቀጣጠልበት ጊዜ ነጭ ጭስ ይመረታል።

2. የሲሊንደር ሄድ መሰንጠቅ ወይም መበላት

በዝገት ወይም በሰበቃ (friction) ምክንያት በሚሰነጠቅበት ጊዜ ኩላንት በዚህ ስንጥቅ በመፍሰስ በተመሳሳይ ኮምበስሽን ቻምበር ዉስጥ በመግባት ከነዳጅ ጋር ሲቀጣጠል ነጭ ጭስ ይመረታል።

3. የሲሊንደር ብሎክ መበላት ወይም መሰንጠቅ

ይህ ኢንጅን ብሎክ ነዳጅ የማቀጣጠል ስራ የሚካሄድበት የሞተር ክፍል ነዉ። ይህ ክፍል ከተሰነጠቀ የኩላንት ፍሳሽ ወደ ሲሊንደር ይኖራል። ከዛም ከነዳጅ ጋር አብሮ ይቀጣጠላል… በዚህ ምክንያት ነጭ ጭስ ይመረታል።

ከነዚህ ዋና ዋና ምክንያቶች በተጨማሪ በናፍጣ መኪኖች ላይ ያለቀ ወይም የተበላ ኢንጀክተር ካለ የናፍጣዉ ጥራት የወረደ ከሆነ እንዲሁም ዝቅተኛ የሲሊንደር እመቃ (compression) ካለ ነጭ ጭስ ይመረታል።

በቤንዚን መኪኖች ደግሞ ከላይ ከጠቀስናቸዉ ምክንያቶች በተጨማሪ የቱርቦ ቻርጀር ብልሽትና የሞተር ፒስተን ቀለበቶች ብልሽት ለዚህ ችግር መንስኤዎች ናቸዉ።

???? የማቀዝቀዣ ፈሳሽ (coolant) ሊክ አደረገ ማለት የማቀዝቀዝ ስርዓት (cooling system) በአግባቡ አይካሄድም ማለት ነዉ።

ይህ ማለት ደግሞ ሞተር ከመጠን በላይ ይሞቃል (engine overheating) ይከሰታል። ይህም ሞተር እንዲነክስ የሚያደርግ ትልቅ ችግር ነዉ ከፍተኛ ወጭም ሊያስወጣን ይችላል ስለዚህ ነጭ ጭስ ካየን በፍጥነት ለባለሙያ ማሳየት።

ባለሙያዉ ደግሞ ከላይ የጠቀስናቸዉን ክፍሎች ማረጋገጥ ይኖርበታል።

ከዚህ በተጨማሪ ሁል ጊዜም ከማሽከርከራችን በፊት የማቀዝቀዣ ፈሳሽ መጠንን (coolant level) ቼክ ማድረግ አለብን።

ማስታወሻ ‼️????

ነጭ ጭስ ችግር የማይሆንበት ሁኔታ!

ሞተር በምናስነሳበት ጊዜ የጭስ ማውጫ (exhaust system) መስመር ላይ በጤዛ መልክ (condense የሆነ) ዉሀ ይኖራል። ሞተር ተነስቶ የሞቀዉ የተቃጠለ አየር ይህን ዉሀ እንዲተን ያደርገዋል ስለዚህ በምናስነሳበት ጊዜ ከ5 እስከ 10 ደቂቃ ድረስ ይህ ነጭ ጭስ የውሃ ትነት ሊሆን ይችላል።

ይህ ጤዛ የሚሆን ዉሀ ከየት ነዉ የሚመጣዉ?

የጭስ ማውጫ (exhaust system) መስመር ላይ ካታላይቲክ ኮንቨርተር (catalytic converter) የምንለዉ ክፍል ያለ ሲሆን ከሞተር የሚወጣዉን በካይና መርዛማ ጋዝ ኦክሲዳይዝ በማድረግ ጉዳቱ እንዲቀንስ የሚያደርግ ነዉ።

nitrogen oxide (nox), carbon monoxide እና hydrocarbon የተሰኙ በካዮችን ወደ nitrogen፣ carbon dioxide እና water vapour ይቀይራል።
ስለዚህ ይህ የውሃ ትነት ጭስ ማውጫ (tail pipe) ላይ በጤዛ መልክ ይሰበሰባል።

ይህ ሁኔታ ተፈጥሯዊ እንጂ በተሽከርካሪው ብልሽት የሚመጣ አይደለም:: ይህ ነጭ ጭስ ከ10 ደቂቃ በላይ ከቀጠለ ግን ከላይ ከጠቀስናቸው ችግሮች አንዱ ሊሆን ስለሚችል ማረጋገጥና መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል።

ከዚህ ቀደም ስለ ጥቁር ጭስ ያቀረብነውን ማብራሪያ ይመልከቱ!????????

ዘወትር ማክሰኞ ከሰዓት አውቶ ቅምሻን ይከታተሉ!