ከአየር ብክለት ነፃ የሆነ የአውሮፕላን ነዳጅ በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገለጸ

ግንቦት 6/2015 (ዋልታ) ከአየር ብክለት ነፃ የሆነ የአውሮፕላን ነዳጅ በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ ግርማ ዋቄ እና የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የአውሮፕላን ነዳጅ በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩን አረጋግጠዋል።

አየር መንገዱ እ.አ.አ በ2050 በዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ማኅበር ሁሉም አየር መንገዶች ወደ አየር የሚለቀቀውን ካርቦን ዜሮ ለማድረግ የተያዘውን ዕቅድ ቀድሞ ማሳካት በሚያስችል ቁመና ላይ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪውን ተለዋዋጭ ምህዳሮች በመቃኘት ከወቅቱ ጋር የሚራመድ ዘመናዊ አሠራር እየተከተለ መሆኑን የቦርድ ሰብሳቢው ገልጸዋል።

በዚህም የአየር ብክለት ተጽዕኖ የሌለው የአውሮፕላን ነዳጅ በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችል ጥናት ተጠናቋል ብለዋል።

ከጥናቱ በመቀጠልም ከሚመለከታቸው የመንግሥትና የግል ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተገብቷል ያሉት የአየር መንገዱ ቦርድ ሰብሳቢ ግርማ ዋቄ ለስኬቱም የቦይንግ፣ የኤር ባስ እና የአያታ የአውሮፕላን ኩባንያዎች እገዛ እያደረጉልን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ከአየር ብክለት ነፃ የሆነውን የአውሮፕላን ነዳጅ በአገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።

አየር መንገዱ ከነዳጅ አቅራቢ ድርጅቶችና ከቴክኖሎጂ ተቋማት ጋር በቅርበት እየሰራ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

ከአየር ብክለት ነፃ የሆነ የአውሮፕላን ነዳጅ ከመኖ ተረፈ ምርት የሚዘጋጅ ሲሆን በየህይወት ዑደት ተፈጥሮን በማዛባት የሚደርሰውን የካርቦን ልቀት የሚያስቀር ይሆናል።

ከተለያዩ ተረፈ ምርቶች የሚመነጭ ከአየር ብክለት ነፃ የሆነ የአውሮፕላን ነዳጅ ሰስቴነብል አቪዬሽን ፊዩል /ሳፍ/ ተብሎ ይጠራል።