የመገናኛ ብዙሃን አንድነትና አብሮነትን የሚሰብኩ፣ ለእዉነት የቆሙ መሆን ይገባቸዋል – ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል

ግንቦት 12/2013 (ዋልታ) – ሁሉም የመገናኛ ብዙሃን የህዝቡን ፍላጎት ለይተው የሚሰሩ አንድነትና አብሮነትን የሚሰብኩ፣ ለእዉነት የቆሙ መሆን ይገባቸዋል ሲሉ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት  ካሚል ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ከ”ፍሬድሪክ ኤርበርት ሰቲፍተንግ” ጋር በትብብር  ያዘጋጀው መገናኛ ብዙሃን ለሰላም፣ ለአብሮነትና ለሃገር  ግንባታ በሚል ርዕሰ  ሀገራዊ የምክክር መድረክ እየተካሄደ  ነው።

የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትርና የባለስልጣኑ የቦርድ ሰብሳቢ ሙፈሪያት  ካሚል ሃላፊነት የሚሰማቸዉ ለሀገር ግንባታና ለሰላም የሚሰሩ መገናኛ ብዙሃን በተጠናከሩ ቁጥር በሁሉም ዘርፍ የሚኖራቸዉ ሚና የማይተካ ይሆናል ሲሉ አንሰተዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ሀገር የማፍረስም የማዳንም ሃይል አላቸዉ ያሉት ሚኒስትሯ  በተለይም ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት የዲሞከራሲ ሽግግር ወቅት ሚናቸዉ የጎላ በመሆኑ ሃላፊነታቸዉን መወጣት እንዳለባቸው ገልፀዋል።

በመድረኩ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሃመድ ኢድሪስ በበኩላቸው መገናኛ ብዙሃን በህዝብ የተጣለባቸውን ሃላፊነት የሚወጡ ለሰላም፣ ለአብሮነት፣ ለሀገር ግንባታና ለዴሞክራሲ የሚሰሩ የህዝቡን ድምፅ ያለ አድሎ የሚያሰሙ መሆን አለባቸው ብለዋል።

የመገናኛ  ብዙሃን ለሰላምና አብሮነት ያላቸውን ሚና የሚያትት መነሻ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ነው።

በምክክር  መድረኩ የመገናኛ ቡዙሃን ሃላፊዎች፣ ባለሞያዎች፣ ሙሁራንና ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች ተገኝተዋል።

(በህይወት አክሊሉ)