ሐምሌ 12/2013 (ዋልታ) – በ290 ሚሊየን ዶላር የሚተገበረው የምስራቅ አፍሪካ ክህሎት ለቀጣናዊ ሽግግር እና ውኅደት (EASTRIP) ፕሮጀክት አፈፃፀም እየተገመገመ ነው።
መርሃግብሩ ከጥቅምት 2011 ዓ.ም ጀምሮ በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ በኢትዮጵያ፣ ኬንያና ታንዛኒያ ገቢራዊ እየተደረገ ሲሆን፣ ዋና ዓላማውም የምስራቅ አፍሪካ የቴክኒክና ሙያ የልህቀት ማዕከላት ግንባታን መከወን ነው ተብሏል።
በዚህም አገራቱ በመረጧቸው አካባቢዎች የምስራቅ አፍሪካ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ማዕከላትን ግንባት እያስጀመሩ ይገኛሉ። በዚህም የቴክኒክና ሙያ ትምህርት አቅርቦትና ጥራትን ማሳደግ ግብ ሆኖ ተቀምጧል።
ፕሮጀክቱ ለሥራ ብቁ የሆነና በትምህርቱ ዓለም የተሰማራ ሰፊ የሰው ኃይል እንዲሁም ነፃ የሰዎችና የንግድ እንቅስቃሴ እየተጀመረ ባለበት የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የሚተገበር መሆኑም ውጤታማ እንደሚያደርገው ተስፋ ተጥሎበታል።
በሂልተን አዲስ አበባ ሆቴል እየተካሄደ ባለው የግምገማ መድረክ የሦስቱ አገራት የፕሮጀክቱ አስፈፃሚ ልዑኮች ባሳኳቸውና ፈተና በሆኑባቸው ጉዳዮች ላይ እየመከሩ ይገኛሉ።
ሦስቱም አገራት መርሃግብሩን ከማስፈፀም አንፃር የሚቀሯቸው የቤት ሥራዎች በርካታ መሆናቸውን ተገንዝበው ጥረት እንዲያደርጉና ለችግሮችም ፈጣን መፍትሔን እየሰጡ እንዲያስፈፅሙ አቅጣጫ ተሰጥቷል።
(በስንታየሁ አባተ)