ጽህፈት ቤቱ በግድቡ ድርድር የተገኘውን የዲፕሎማሲ ድል በሕዝባዊ ተሳትፎ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ

ዶክተር አረጋዊ በርሄ

ሐምሌ 12/2013 (ዋልታ) – የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት በግድቡ ድርድር የተገኘውን የዲፕሎማሲ ድል በሕዝባዊ ተሳትፎ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።

የፀጥታው ምክር ቤት የህዳሴው ግድብ በአፍሪካ ህብረት እንዲታይ ሲል ያሳየውን ድጋፍ በሕዝባዊ ተሳትፎ አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ ገልጸዋል።

ዶክተር አረጋዊ የህዳሴው ግድብ ድርድር ወደ አፍሪካ መምጣቱን ተከትሎ በህዝብ ዘንድ የተፈጠረውን መነቃቃት በተደራጀ መልኩ ለግድቡ ግንባታ አቅም እንዲሆን ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

”ትስስር ለህዳሴ ግድብ” በሚል መሪ ሀሳብ ህዝቡን በማደራጀት አስተዋጽኦ እንዲጨምር ለማድረግ በሀገር ውስጥም በውጪም ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፤ በአንድነት መስራት ውጤት የሚያመጣ በመሆኑ ለወደፊትም ይህ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

አሁን የተገኘውን የዲፕሎማሲ ድል ለማስቀጠል ጠንክሮ መስራትና የህዝቡን ተሳትፎ በየዘርፉ ማሳደግ ያስፈልጋል ያሉት ዋና ደይሬክተሩ፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያን ወዳጆች በማደራጀት ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን እንዲቀጥሉ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ መናገራቸውን ኢፕድ ዘግቧል።