የአሜሪካ የእርዳታ ፕሮግራምን እንዲመሩ እጩ የሆኑ የመጀመሪያው አፍሪካዊ

መስከረም 18/2014 (ዋልታ) የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር (ሲዲሲ አፍሪካ) ኃላፊ የሆኑትን ዶክተር ጆን ንኬንጋሶንግ ኤችአይቪ/ኤድስ መከላከል ላይ የሚያተኩረውን የሕብረተሰብ ጤና ፕሮግራምን (ፔፕፋር ፕሮግራም) እንዲመሩ በእጩነት አቅርበዋል።

ፕሮግራሙ የፕሬዝዳንቶች የድንገተኛ ጊዜ እቅድ የማገገሚያ እርዳታ እንደሚሰኝም ተጠቅሷል፡፡

የሰባት ቢሊየን ዶላር በጀት የተያዘለት ይህ ፕሮግራም መንግስታት ኤችአይቪ በደማቸው ላለባቸውን ሰዎች የገንዘብ ድጋፍና የህክምና አገልግሎት እንዲያቀርቡ ይሰራል፤ አብዛኞቹም ከሰሃራ በታች ያሉ አገራ ውስጥ የሚገኙ ናቸው ተብሏል፡፡

ሹመቱ ከፀደቀ የካሜሮን ተወላጅ የሆኑት ዶክተር ንኬንጋሶንግ ከአፍሪካ ፕሮግራሙን የሚመሩ  የመጀመሪያው ሰው ይሆናሉ፡፡

ዶክተሩ እ.አ.አ በ2013 ይህን ፕሮግራም ከመሰረቱት ሰዎች አንዱ ሲሆኑ፣ በአሜሪካን የሚመራው ይህ ፕሮግራም ካሳለፍነው የካቲት ወዲህ ያለመሪ ቆይቷል፡፡ የቀድሞው መሪ ዲቦራህ ቢሪክሰ በአሜሪካ ኮሮናን መከላከል ዘመቻን በመቀላቀል ኃላፊነታቸውን ለቀዋል፡፡

የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ኤችአይቪ እየጨመረ መምጣቱን ቢቢሲ ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኤክስፐርቶች እንደሚሉት፤ ብዙ ሰዎች ኤችአይቪ እየተመረመሩ አይደለም፤ ሌሎችም በመድኃኒት አቅርቦት መቆራረጥ መድኃኒት በአግባቡ አይወስዱም፡፡

የተባበሩት መንግስታት የእርዳታ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዋይን ቢያኒያማ “በእጩነት የቀረቡት ዶክተር ንኬንጋሶንግ ኤች አይቪን በመዋጋት የረዥም ጊዜ ልምድ አላቸው ታላቅ አጋራችንም ናቸው” ብለዋል፡፡

ብዙ አጋሮቻቸው ደስታቸውን እየገለፁ ቢሆንም፤ ሌሎች ደግሞ አፍሪካ ፍትሃዊ የኮቪድ-19 ክትባት ስርጭት እንድታገኝ እየሰሩ ባሉበት ወቅት መሆኑ ጥያቄ ፈጥሮባቸዋል፡፡