በኮቪድ-19 ከፍተኛ የሞት መጠን የተመዘገበበት ሳምንት

ዶ/ር ጽጌረዳ ክፍሌ

መስከረም 18/2014 (ዋልታ) የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ጀምሮ ባለፈው ሣምንት የተመዘገበው የሞት መጠን ከፍተኛው መሆኑን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጽጌረዳ ክፍሌ ዛሬ በሰጡት መግለጫ “አዲሱ የኮቪድ-19 ዝርያ (ዴልታ) ቫይረስ በኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰራጨ ነው” ብለዋል።

ከመስከረም 10 እስከ 16 ቀን 2014 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ ከተመረመሩ 57 ሺሕ 940 ሰዎች መካከል 8 ሺሕ 753 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፣ የመያዝ ምጣኔውም 15 በመቶ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሎችም የመያዝ ምጣኔው ከአገር አቀፍ የመያዝ ምጣኔ ከፍ ብሎ መታየቱን ጠቁመው፤ በሣምንቱ በአገር አቀፍ ደረጃ በኮቪድ-19 ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 271 እንደነበር ገልጸዋል።

በዚሁ ሣምንት ከ798 በላይ ታማሚዎች ወደ ጽኑ ሕክምና ማዕከል ገብተው ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑንም ጠቁመዋል።

“በአዲስ አበባና በአንዳንድ የክልል ከተሞች የታካሚዎች ቁጥር በመጨመሩ የጽኑ ሕክምና ክፍሎች ሞልተው ታካሚዎች ለከፍተኛ ችግር እየተጋለጡ ነው” ብለዋል።

በወረርሽኙ የመያዝ፣ የሞት እና የጽኑ ሕሙማን ቁጥር መጨመር የአዲሱ ኮቪድ-19 ዴልታ ቫይረስ ስርጭት ከፍተኛ መሆኑን እንደሚያሳይ ጠቁመዋል።

“የኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶች ተግባራዊ አለመደረጋቸው እና የክትባት ሽፋን ዝቅተኛ መሆንም ለስርጭቱ መስፋፋት በምክንያት የሚጠቀሱ ናቸው” ብለዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ በተመረጡ 14 ከተሞች በተደረገ ጥናት የመከላከያ መንገዶች አተገባበርን ዝቅተኛ መሆኑንና በኅብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ መዘናጋት መኖሩን ማወቅ መቻሉን ገልጸዋል።

“ለወረርሽኙ ፖለቲካዊ አንድምታ መስጠት፣ በየደረጃው ያሉ አመራሮች ዓርአያ ሆነው አለመገኘት፣ በየደረጃው የተዋቀሩ ግብረ ሀይሎች መመሪያ የማስፈጸም ተሳተፎ እያነሰ መምጣት ኅብረተሰቡ የመከላከያ መንገዶችን እንዳይተገብር ምክንያቶች ሆነዋል” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ኅብረተሰቡ አሁንም ወረርሽኙ የሚያስከትላቸውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሶች በመገንዘብ ያለመሰልቸት የመከላከያ መንገዶችን እንዲተገብርም አሳስበዋል።

ሕይወታቸው ካለፈ መካከል አብዛኞቹ ያልተከተቡ መሆናቸውን የገለጹት ዶክተር ጽጌረዳ፤ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች መከተብ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

መገናኛ ብዙኃን፣ የመንግስትና የግል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና ኃላፊነት የተጣለበት ግብረኃይል ለወረርሽኙ ትኩረት በመስጠት የድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።