የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ከተመድ የኢትዮጵያ ተጠሪ ጋር በሰብዓዊ ድጋፍ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ

ነሐሴ 17/2015 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተ/ማሪያም (ዶ/ር) እና አመራሮች አዲስ ከተሾሙት የተባሩት መንግስታት የኢትዮጵያ ተጠሪና የሰብአዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር) ጋር በሰብዓዊ ድጋፍ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

ኮሚሽነሩ በኢትዮጵያ ስላለው የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ክፍተትና በኢትዮጵያ መንግስትና በተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲዎች መካከል ስላለው ተቀራርቦ የመስራት ልምድ ለአዲስ ተሿሚው ገለጻ አድርገውላቸዋል፡፡

የተመድ ተጠሪው በበኩላቸው በኢትዮጵያ በሚኖራቸው የስራ ቆይታ የነበረውን ተቀራርቦ የመስራት ልምድ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስና የሰብዓዊ ድጋፉን ክፍተት ለመሙላት በሚያስፈልገው ሁሉ ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆናቸውን መግለጻቸውን ከአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡