የኢትዮጵያ መንግስትና የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ እርዳታ ዳግም በአፋጣኝ ለማስጀመር የጋራ ትብብራቸውን እንደሚያጠናክሩ ገለጹ

ነሐሴ 17/2015 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ መንግስትና የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ እርዳታ ዳግም በአፋጣኝ ለማስጀመር የጋራ ትብብራቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስትና የተባበሩት መንግስታት ተወካይ የኢትዮጵያ ቡድን በአስቸጋሪ ሁኔታ ለሚገኙ ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ ዳግም በፍጥነት እንዲጀመር የጋራ ጥረቶቻቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታወቀዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከተ.መ.ድ የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብአዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ራሚዝ አላክባሮቭና (ዶ/ር) የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት(ኦቻ) የኢትዮጵያ ተወካይ ሚሼል ሳድን ጨምሮ ከሌሎች የድርጅቱ የኢትዮጵያ ቡድን ተወካዮች ጋር ገንቢና ፍሬያማ ውይይት ካደረጉ በኋላ የጋራ መግለጫ ማውጣታቸው ተገልጿል።

ከውይይቱ በኋላ የኢትዮጵያ መንግስትና የተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ ተወካዮች ባወጡት የጋራ መግለጫ ሁለቱ ወገኖች ትብብራቸውን ለማጠናከርና በኢትዮጵያ አካታችና ዘላቂ ልማት ለማምጣት በጋራ እንደሚሰሩ አስታውቀውል።

በኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ለሚገኙ ማህበረሰቦች የሰብዓዊ እርዳታ በአፋጣኝ በድጋሚ እንዲጀመር የጋራ ጥረታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ማመልከታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።