የኢትዮጵያ አምባሳደሮች የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስን ጎበኙ

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ

ታኅሣሥ 11/2015 (ዋልታ) በተለያዩ በውጭ ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የሪፎርም ሥራዎችን ጎበኙ።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል እና የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት ሊቀመንበር ደመላሽ ገ/ሚካኤል ለአምባሳደሮቹ በፖሊሳዊ ሥነ-ሥርዓት ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

ኮሚሽነር ጀነራሉ የለውጡ መንግስት ለሪፎርሙ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠቱ በተከናወነው ተጨባጭ የለውጥ ተግባር አሁን ላይ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኢትዮጵያን በሚመጥን ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረዋል፡፡

አምባሳደሮቹን ወክለው ንግግር ያደረጉት በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች እጅግ መደሰታቸውን ተናግረው በአጭር ጊዜ ውስጥ የፖሊስ ሠራዊታችን እድገት እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ ተስፋ ሰጪ ሆኖ አግኝተነዋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ያደጉ ሀገራት ፖሊስ የደረሰበት ደረጃ ላይ እንደሚደርስና ለሀገራችንና ለህዝባችን ሰላም ትልቅ ዋስትና ሊሆን እንደሚችል እምነታችን ነው ያሉት አምባሳደሩ ”እናንተ በዚህ መስክ ተሰማርታችሁ ሌት ተቀን የህዝባችሁን ደህንነት የምትጠብቁ የፖሊስ ሠራዊት አባላት በሙሉ ለሀገራችን የሰላም ዋስትና መሆናችሁን አረጋግጠናል” ብለዋል።

አምባሳደሮቹ በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ባለፉት አራት ዓመታት የተከናወኑ ተጨባጭ የሪፎርም ስራዎችን ተዘዋውረው መመልከታቸውን ከተቋሙ የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡