የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ በሲያትል ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ተወያየ

ሚያዝያ 16/2013 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት የተመራ የልዑካን ቡድን በሲያትልና አካባቢው ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት አድርጓል::

ዳይሬክተሯ በሲያትልና አካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያን ለሀገራዊ ፕሮጀክቶችና ወቅታዊ ጥሪዎች ለሰጡት ምላሽ ያላቸውን አክብሮት ገልጸዋል፡፡

በሎስ አንጀለስ የኢፌዴሪ ቆንስል ጄነራል አምባሳደር ሙሉጌታ ከሊል በበኩላቸው በሲያትልና አካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለልዩ ልዩ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰው፣ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጽ/ቤቱ ከዳያስፖራው ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

ተሳታፊዎችም በኤጀንሲው በሚሰጠው አገልግሎትና አደረጃጀት ደስተኛ መሆናቸውን፣ ዳያስፖራው ልጆቹን ስለኢትዮጵያ በማስተማር የሀገራቸው አምባሳደር ሊያደርጋቸው እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ዳያስፖራውን የተመለከቱ የህግ ማዕቀፎች በሚወጡበት ወቅት ሀሳባቸው መካተት እንዳለበት፣ የውጭ ምንዛሪ ክምችት እንዲያድግ ዳያስፖራውን የሚያበረታቱ አሰራሮች መጠናከር እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

የህግ የበላይነትን ከማስከበር አንጻር በመንግስት በኩል ተጨማሪ ጥረቶችን ማድረግ እንደሚገባ እንዲሁም ዳያስፖራው በማንኛውም ሁኔታ ለሀገሩ ዘብ መቆም እንዳለበት ማሳሰባቸውን ከውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ጽ/ት ቤት የተገኘው መረጃ አመላክቷል።