የዓለም ምግብ ፕሮግራም የሰብአዊ ድጋፉን በድርቅ ወደ ተጎዱ አካባቢዎችም እንደሚያስፋፋ ገለጸ

ሚያዝያ 22/2014 (ዋልታ) የዓለም የምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ የሚያደርገውን የሰብአዊ ድጋፍ በድርቅ ወደ ተጎዱ አካባቢዎች እንደሚያስፋፋ በተቋሙ የኢትዮጵያ ተጠሪ ዳይሬክተር ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በቅርቡ አዲስ ከተሾሙት የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተጠሪ ዳይሬክተር ክላውድ ጂቢዳር ጋር ዛሬ በጽሕፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የተሻለ ሥራዎችን ማከናወኑን የገለጹት ሚኒስትሩ በትግራይ ክልል በከባድ ሁኔታ ውስጥም እርዳታ ለሚሹ ዜጎች እያደረገ ያለው ሰብአዊ እርዳታ የሚመሰገን ነው ብለዋል።

አሁን ላይ በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውና እንደ ዓለም ምግብ ፕሮግራም ያሉ ድርጅቶች ሁሉን ዐቀፍ ተደራሽ የሆነ ሰብአዊ እርዳታ በማድረግ የተጠናከረ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በትግራይ ክልል እየሰጠው ካለው ሰብአዊ እርዳታ በተጨማሪ በአማራ እና በአፋር ክልል እንዲሁም ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎችም ተመሳሳይ ሥራ እንዲሰራ ጠይቀዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መንግሥት ያልተገደብ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደረግ ያሳለፈውን ውሳኔ በማክበር የተሻለ ድጋፍ እንዲደረግ እየሰራ መሆኑን አንስተው የሕወሓት ቡድን ግን አሁንም ሰብአዊ እርዳታውን ለማስተጓጎል እየሞከረ ነው ብለዋል። ዓለም ዐቀፍ ለጋሽ አካላትም የቡድኑን አካሄድ ማውገዝ አለባቸው ብለዋል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተጠሪ ዳይሬክተር ክላውድ ጂቢዳር በበኩላቸው የመንግሥትን ቁርጠኝነት በማድነቅ በቀጣይም አብሮ ለመስራት በሙሉ ቁርጠኝነት እንደሚንቀሳቀሱ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ከችግር ውስጥ ወጥቶ ወደ ተሻለ መንገድ እና እድገት መስመር መግባት ከራሷም በላይ ለሌሎች ሀገራትም ትልቅ ሚና ስላለው ከመንግሥት ጎን ሆነን ችግሩን ለማለፍ እንሰራለን ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች የውስጥ መፈናቀል ካጋጠማቸው ዜጎቿ በተጨማሪ ከ900 ሺሕ በላይ ስደተኞችን እያስተናገደች መሆኗን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።

የምግብ አቅርቦት እጥረትን ለመቅረፍ ኢትዮጵያ ስንዴን በከፍተኛ መጠን የማምረት አቅም ያላት ሀገር በመሆኗ ለዚህ ተግባር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ለሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም የሚያደርገውን የሰብአዊ ድጋፍ በድርቅ ወደ ተጎዱ አካባቢዎችም እንደሚያስፋፋ ተናግረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ስንዴ የማምረቱን ጉዳይ በተመለከተ የመንግሥት ትልቁ ትኩረት እና የጀመረው ሥራ መሆኑን አንስተው በቆላማ አካባቢዎች ስንዴን በመስኖ የማምረቱ ሥራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ለዘርፉ ያሳየው ቁርጠኝነት ከመንግሥት ፖሊሲ ጋር የሚስማማ ነው ብለዋል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተጠሪ ዳይሬክተር ክላውድ በኢትዮጵያ የሥራ ቆይታቸው መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው መግለፃቸውን ከውጭ ጉዳ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!