የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት የሀገሪቱን ታላቁን ኒሻን ለፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አበረከቱ

መጋቢት 12/2016 (አዲስ ዋልታ) የደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንትና የጦር ኃይሎች ዋና አዛዥ ሳልቫ ኪር ማያርዲት የሀገሪቱን ታላቁን ኒሻን ለኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አበረከቱ፡፡

ፕሬዝዳንቱ ኢትዮጵያ በቸገረን ጊዜ ሁሉ መጠጊያችን መጠለያችን ከመሆኗም በላይ ለዚህ ሀገራዊ ነፃነታችን ክብር የሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ልጆቿን ህይወት ጭምር በመክፈል እንደሀገር እንድንቆም ያደረጉ ወለታቸውንም መቼም ከፍለን የማንጨርሰው ባለውለታችን ናቸው ብለዋል።

ዛሬም ከጎናችን ያልተለዩና የቁርጥ ቀን ወንድሞቻችን ከመሆናቸውም በላይ በደም የተሳሰርን ማንም ሊፈታው የማይችል የአንድ ቤተሰብ ልጆች መሆናችንን የሚያረጋግጥ ሽልማታችን እንደሆነ መላው የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን ህዝብ እንዲያውቅልን እንፈልጋለን ሲሉም ገልጸዋል።

በተጨማሪም ይህንን ታላቅ ሽልማት ለኢፌዴሪ የመከላከያ ሠራዊት የበላይ ኃላፊና የምስራቅ አፍሪካ ፊልድ ማርሻል ለሆኑት ለፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በደቡብ ሱዳን ህዝብ ስም ሳበረክት ታላቅ ኩራት ይሰማኛል በማለትም ተናግረዋል።

በስነ ሥርዓቱ ላይ የሀገሪቱ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም፣ የሀገሪቱ የደህንነት ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ ጄኔራል መኮንኖችና የኢፌዴሪ መከላከያ ጄኔራል መኮንኖች መገኘታቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡