እንደ ዓድዋው ሁሉ አገራችን የአትሌቲክስ ቤተ መዘክር ያስፈልጋታል

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)

ምክንያተ ጽሕፈት / እንደ መንደርደሪያ

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ ምክንያት የሆነኝ ከሁለት ሳምንት በፊት የዓድዋ ድልን ለመዘከር ከአንድ ሚዲያ ጋር በዓድዋ ሙዚየም በነበረኝ ቃለ መጠይቅ ነው፡፡ እናም ከቃለ መጠይቁ በኋላ እንደ ታሪክና ቅርስ ባለሙያ ሙዚየሙን ለመጎብኘት ዕድሉን አግኝቼ ነበር፡፡ ከዚህ ለኢትዮጵያውያን፣ ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ሕዝብ የነፃነት ትምህርት በሆነው የዓድዋ ሙዚየም አስደናቂና አስደማሚ ጉብኝቴ ፍፃሜ በኋላም፣ እንደ ዓድዋው ሁሉ በዓድዋ የነፃነትና የድል መንፈስ አገራችንን ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ በክብር ከፍ ያደረጉና ሰንደቀ ዓላማዋ እንዲውለበለብ ላደረጉ ጀግኖች አትሌቶቻችንስ የመታሰቢያ ቤተ መዘክር / ሙዚየም አያስፈልጋቸው ይሆን እንዴ? ስል ብቻዬን ቆዘምኩ፡፡

የአትሌቲክስ ቤተ መዘክር / ሙዚየም ጉዳይ ቢታሰብበት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከጥቂት ወራት በፊት የመደመር መጽሐፋቸውን ለየክልል ርዕሳነ መንግሥታት ከአደራ ቃል ጋር በስጦታ አበርክተው እንደነበር እናስታውሳለን፡፡

የዚህ የስጦታው ዐቢይ ምክንያት ደግሞ የየክልሉ ርዕሳነ መንግሥታት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በስጦታ ከተበረከተላቸው መጽሐፍ በሚያገኙት ሽያጭ በየክልላቸው የሚገኙ የአገር ሀብትና ኩራት የሆኑ ታሪካዊ ቅርሶችን እንዲንከባከቡ፣ እንዲያድሱ፣ የሕዝባቸውን ታሪክ፣ ቱባ ባህል፣ ወግና ሥርዓት በሚገባ ሰንደው ለትውልድ እንዲተላለፍ፣ እንዲሁም ለታዳጊዎችና ለወጣቶች መዝናኛ ማዘውተሪያ የሚሆኑ ማዕከላትን እንዲገነቡ ነበር፡፡

በዚሁ መሠረትም የየክልል መንግሥታት ከመደመር መጽሐፍ ባገኙት ገቢ በርካታ ሥራዎችን ማከናወናቸውን ከመገናኛ ብዙኃን ተከታትለናል፡፡ ሁሉንም መዘርዘር ባይቻልም ለአብነት ያህል ለመጥቀስም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አበቤ ከመደመር መጽሐፍ በተገኘው ገቢ በየክፍለ ከተማው ለታዳጊዎችና ለወጣቶች የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችንና የመዝናኛ ማዕከላትን በአጭር ጊዜ አስገንብተው ለሕዝቡ አስረክበዋል፡፡

ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ በከተማችን ዕምብርት ፒያሳ ላይ እንደ የዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም ያሉ ለኢትዮጵያ፣ ለአፍሪካ፣ ለአፍሪካ አሜሪካውያን፣ ለመላው ጥቁር ሕዝብና በአጠቃላይም ነፃነታቸውን ለሚያፈቅሩና ለሚያከብሩ የሰው ልጆች ሁሉ የነፃነት ትምህርትና ሰው የመሆን ክብርና ፍቅር ቋሚና ህያው የሆነ አሻራ አቁመውልናል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እና ከከንቲባ አዳነች ጀምሮ ሐሳቡን ካመነጩት፣ ሐሳቡን ተግባራዊ ያደረጉት አርትቴክት እስክንድር ውበቱና በዚህ ታላቅ ታሪካዊ ሙዚየም ግንባታ በእያንዳንዱ ሥራ ላይ የተሳተፉ ሁሉ ክብር ይገባቸዋል፡፡

አትሌቲክስ ዳግማዊ ዓድዋችን

እንደ ዓድዋው ድል ሁሉ አትሌቲክስ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ሁሉ የብሔራዊ ኩራት ምንጭና በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በተደጋጋሚ በክብር ከፍ እንዲል ያደረገና አሁንም እያደረገ ያለ ሌላኛው ዳግማዊ ዓድዋችን ነው፡፡

ታሪክ እንደሚነግረን ሻምበል አበበ በቂላ በሮማ ኦሊምፒክ በባዶ እግሩ ሮጦ ማራቶንን ሲያሸንፍ የዓለም የመገናኝ ብዙኃን በአንድ ድምፅ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ዳግመኛ ዓድዋን በሮም አደባባይ ደገመችው፤›› ተብሎ ነው የተጻፈው፣ የተነገረው፡፡

ጀግናው አበበ በቂላ በሮም ኦሎምፒክ በባዶ እግሩ ሮጦ የማሸነፉ አንፀባራቂ ድል ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን በዓድዋ ዓውደ ግንባር ለእግራቸው መጫሚያ ሳይኖራቸው በባዶ እግራቸው ዘምተው ጣሊያንን ድል የማድረጋቸውን ያን የዘመን ታላቅ ክስተት የሆነ ታላቁን የዓድዋን ታሪካዊ የነፃነት ተጋድሎ በክብር ያስታወሰ፣ በክብር የዘከረ ነበር፡፡

በሻምበል አበበ ቢቂላ አሀዱ የተባለው የኢትዮጵያውያን የኦሊምፒክ የድል ብሥራት ሌሎች በርካታ ጀግኖችን ወልዷል፡፡ ዋሚ ቢራቱ፣ ማሞ ወልዴ፣ ምሩፅ ይፍጠር፣ በላይነህ ዴንሳሞ፣ ገዛኸኝ አበራ፣ ገብረ እግዚአብሔር ገብረ ማርያም፣ ጀግናው ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ስለሺ ስኅን፣ ወዘተ በዓለም አደባባይ የአገራችንን የኢትዮጵያን ስም በክብር እንዲጻፍ ያደረጉና ሰንደቅ ዓላማዋም በድል እንዲውለበለብ ያደረጉ የሁልጊዜም ጀግኖቻችን ናቸው፡፡

በሴቶች አትሌቲክስም በሴት የ10 ሺሕ ሜትር የኦሎምፒክ ውድድር የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት የወርቅ ሜዳሊይ አሸናፊ የሆነችው ፍልቅልቋ፣ የሰላም እናት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፣ የማራቶን ጀግናዋ ብርሃኔ አደሬ፣ መሠረት ደፋር፣ ተዓምረኞቹ የዲባባ ቤተሰቦች እጅጋየሁ፣ ጥሩነሽና ገንዘቤ ዲባባ፣ በቅርብ ጊዜ ደግሞ ተደጋጋሚ ድልን በማስመዝገብ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በክብር ከፍ እያደረጉ ያሉት ጉዳፍ ፀጋይና ለተሰንበት ግደይ፣ ወዘተ የሁላችንም ኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ኩራት፣ ትልቅ ክብር ናቸው፡፡

ሃያ ሰባት ጊዜ ሪከርዶችን የሰባበረውና ‹‹ልዩ ፍጥረት ነው›› እስኪባል ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ክብርና ዝናን ያተረፈው የጀግናችን የሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ድል፣ እንደ ማንዴላ ያሉ ታላቅ የነፃነት ታጋይና አርበኛ ልብን በነፃነት የድል መንፈስ ያሞቀና ያስደነቀ ነው፡፡ ይህን በደቡብ አፍሪካ በዩኒቨርሲቲ ትምህርትና በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በነበረኝ ቆይታዬ ወቅት በሚገባ አረጋግጫለሁ፡፡//////

በአጭር ቃል ለመግለጽም ጀግናው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ ‹‹He is an International Brand of Ethiopia!!››. እንደ አንበሳው ቀነኒሳ በቀለ ያለ ጀግና አትሌታችን ደግሞ አገራችን ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየነባች ካለችው ግድብ ጋር በተያያዘ በፈረንሣይ ፓሪስ ውስጥ ግብፃውያንን ዲፕሎማቶችን ያሳፈረና ድል ያደረገ፣ የአትሌቲክስ ዲፕሎማትና አምባሳደራችን ነው፡፡

እንዲያውም መንግሥት ወደፊት በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በኩል ‹የአትሌቲክስ ዲፕሎማሲ› ቡድን ቢያቋቋም ጥሩና አዋጭ ነው እላለሁ፡፡

እንግዲህ እነዚህና በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ያልጠቀስኳቸው በርካታ የኢትዮጵያ ኩራትና ክብር የሆኑ አትሌቶቻችንን ድሎቻቸው፣ ገድሎቻቸው፣ ትዝታቸው፣ ታሪካዊ ፎቶግራፎቻቸው፣ ሽልማቶቻቸው፣ ወዘተ በክብር ተጠብቀው ለኢትዮጵያውያን፣ ለአፍሪካውያንና ለመላው ዓለም የምናሳይበት የአትሌቲክስ ቤተ መዘክር/ሙዚየም ያስፈልገናል፡፡

እንዲያው አንድ ጎብኚ/ቱሪስት እስቲ እናንተ ኢትዮጵያውያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ስማችሁንና ሰንደቅ ዓላማችሁን በክብር ከፍ ያደረጉ የአትሌቲክስ ጀግኖቻችሁን የሻምበል አበበ ቢቂላን፣ የዋሚ ቢራቱን፣ የምሩፅ ይፍጠርን፣ የማሞ ወልዴን፣ የበላይነህ ዴንሳሞን፣ የሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴን፣ የገብረ እግዚአብሔር ገብረ ማርያምን፣ የእነ ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉን፣ የጥሩነሽን፣ የእጅጋየሁና የገንዘቤ ዲባባን፣ የጌጤ ዋሚን፣ የለተሰንበት ግደይን፣ ወዘተ ታሪክ የሚዘክር ምን መታሰቢያ አላችሁ እስቲ አሳዩን ብንባል ምን እንላለን!!

እናም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐበይ (ዶ/ር) እና ክብርት ከንቲባ አዳነች የመላው የኢትዮጵያውያን፣ የአፍሪካውያንና የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ኩራት ለሆነው ለዓድዋው ድል መታሰቢያ እንደተገነባው ሁሉ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአገራችንን ሰንደቅ ዓላማ በክብር ከፍ እንዲልና በድል እንዲውለበለብ ላደረጉት አትሌቶቻችን የኢትዮጵያን/ የዓድዋን የነፃነትና የድል መንፈስ በአፍሪካና በመላው ዓለም ለናኙ ጀግኖች፣ አትሌቶቻችን በመዲናችን በአዲስ አበባ ትልቅ ቤተ መዘከር/ሙዚየም ያስፈልጋቸዋል፡፡

ሰላም ለኢትዮጵያ!