የደቡብ ክልል በድርቅ ለተጎዱ የሶማሌ ክልል አካባቢዎች የ20 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ

ጥር 12/2014 (ዋልታ) የደቡብ ክልል በድርቅ ለተጎዱ የሶማሌ ክልል አካባቢዎች የ20 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ፡፡

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እርስቱ ይርዳ ከክልሉ መንግስት የተደረገውን ድጋፍ ባስረከቡበት ወቅት እንደገለጹት የሶማሌ ሕዝብ ኢትዮጵያ ጸንታ እንድትቆይ ከፍተኛ ዋጋ የከፈለ ሕዝብ ነው።

የኢትዮጵያን ድንበር አካባቢዎችን በመጠበቅ ለኢትዮጵያ እየከፈለ ካለው ዋጋ አንጻር ብዙ መልማት ይኖርበታል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።

ይህን ሕዝብ ችግር ሲያጋጥመው መላው ኢትዮጵያውያን አለውልህ ሊለው ይገባልም ብለዋል።

በተፈጥሮ ድርቅ ባጋጠመው አደጋ የክልሉ መንግስት አለኝታነቱን ለመግለጽ ለመጀመሪያ ዙር 5 ሚሊየን ብር የሚያወጣ የአይነት እና 15 ሚሊየን ብር በካሽ በድምሩ የ20 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረግ መቻሉንም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።

የሁለቱን ክልል ሕዝቦች ትስስር ለማጠናከር እንደሚሰራም መግለጻቸውን ከደቡብ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ የደቡብ ክልል ያጋጠመንን ችግር በመረዳት ላደረገልን ድጋፍ ምስጋናችን የላቀ ነው ብለዋል።

የክልሉ መንግስት ካለው ውስን ሀብት ቀንሶ ያደረገልን ድጋፍ በሁለቱ ክልል ሕዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ያጠናክራል ሲሉም ጠቁመዋል።

የሱማሌ ክልል በሀገሪቱ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለማስከበር ወደ 3 ቢሊየን ብር ወጪ አድርጓል በማለት ተናግረዋል።

የተደረገልን ድጋፍ ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በዝናብ እጦት ምክንያት ያጋጠመን አደጋ ከፍተኛ እንደሆነና ይህንንም ለመቋቋም ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተደረገ ነው ብለዋል።