የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በኢትዮጵያ እንዲካሄድ መወሰኑ ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

ጥር 12/2014 (ዋልታ) 35ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በኢትዮጵያ እንዲካሄድ መወሰኑ ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።

ቃል አቀባዩ የኅብረቱ የመሪዎች ስብሰባ በኢትዮጵያ እንዳይካሄድ በርካታ አሻጥሮች ሲደረጉ እንደነበርም ተናግረዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መኖር እና በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ጦርነት መነሻ አድርጎ በኢትዮጵያ ሰላም የለም በሚል ምክንያት የኅብረቱ ስብሰባ እንዳይደረግ የተለያዩ ጫናዎች እየተደረገ ነበርም ብለዋል።

የኅብረቱ ስብሰባ በኢትዮጵያ መካሄዱ ኢትዮጵያ አሁንም ዓለም ዐቀፍ ስብሰባ ማከናወን እንደምትችል የሚያሳይ ይሆናል ተብሏል።

የኅብረቱን የመሪዎች ስብሰባ በተለየ መልኩ ለማከናወን ዝግጅቶች እየተደረጉ ይገኛልም ብለዋል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ።

በሳምንታዊው መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከካናዳው አቻቸው ጀስቲን ቱሩዶ ጋር በስልክ ውይይት ማድረጋቸው ተነስቷል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የኖርዌይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በስልክ ውይይት ማድረጋቸውም ተጠቁሟል።