የጁንታውን ኃይል ለመያዝና ለህግ ለማቅረብ ሠራዊቱ እረፍት የሌለው አሰሳ እያደረገ ነው – ኮ/ል አማረ ሞላ

 

የ12ኛ መተማ ክፍለ ጦር አዛዥ ኮሎኔል አማረ ሞላ የጁንታውን ኃይል ለመያዝና ለህግ ለማቅረብ ሠራዊቱ እረፍት የሌለው አሰሳ እያደረገ እንደሆነ ተናገሩ።

ቀደም ባሉት አጭር ጊዜያት ውስጥ በተሰራው የህግ ማስከበር ሥራ ዋናው የህወሃት ጁንታ ተዋጊ ኃይል በመደምሰሱ ጁንታው በዋሻዎች፣ ሸጦችና ተራራዎች ታማኝ ጠባቂዎችን ይዞ መሸሹን ተከትሎ ሰራዊቱ እየሰራው ባለው ያልተቋረጠ ጠንካራ አሰሳ በርካታ የጁንታው አመራሮች እየተያዙና እየተደመሰሱ እንደሆነም ተናግረዋል።

እየተደረገ ባለው ያልተቋረጠ አሰሳ በርካታ የጁንታው ጠባቂ ታጣቂዎች እጃቸውን እየሰጡ እንደሆነም ክ/ጦር አዛዡ አስታውቀዋል። ቀሪ የጁንታውን አባላት ከገቡበት ጉድጓድ አውጥቶ ለፍርድ ለማቅረብና ለመደምሰስ የሰራዊቱ ተነሳሽነትና ጀግንነት እንደተጠበቀ ነው ብለዋል።

የ3ኛ ብርጌድ አዛዥ ኮሎኔል አልታሰብ መንግስቴ በበኩላቸው፣ ተወንጫፊ ሮኬቶችን ጨምሮ በርካታ የመሳሪያ ክምችት ያለባቸው ዲፖዎችንና መሳሪያ ጎታች ተሽከርካሪዎች እንዲሁም ሌሎች በርካታ ተሽከርካሪዎች በየጫካውና በየሸጡ መገኘታቸውን አረጋግጠዋል።

እጅ አልሰጥም ያለውን ታጣቂ መምታት፣ ዋናውን የጁንታ ሃይል ለህግ ማቅረብ እንዲሁም ጠላት ሲጠቀምባቸው የነበሩና ሊጠቀምባቸው ያሸሻቸውን ንብረቶች መሰብሰብ እንዲሁም በጠላት ፕሮፖጋንዳ አካባቢውን ለቆ የወጣውን ህዝብ ወደ ቀየው እንዲመለስ ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ስራ እኃከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።
(ምንጭ፡- የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር)