አስተዳደሩ ከአዲስ አበባ ሃይማኖቶች ኅብረት ጉባኤ እና ከሰላም ምክር ቤት ጋር ተወያየ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከአዲስ አበባ ሃይማኖቶች ኅብረት ጉባኤ እና ከሰላም ምክር ቤት ጋር በከተማዋ ሰላም ላይ ውይይት ማድረጉን ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

በአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና አሁናዊ ሁኔታ ላይ ከሀይማኖት አባቶችና ከሰላም ምክርቤት አባላት ጋር ውይይት ተካሂዷል።

በውይይቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እና የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ መለሰ አለሙ ተገኝተዋል።

ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሰላም በምኞት ሳይሆን ከትናንቱ በመማርና በመስራት እንደሚረጋገጥ ጠቁመው ለውጡ በሁሉም ተሳትፎ የመጣ፣ ሁሉንም አካታች፣ ሁሉንም የሚጠቅም መሆኑንም ተናግረዋል።

በከተማዋ ሰላም እና ድህንነትን ለማረጋገጥ የነዋሪዎች እና የሃይማኖት ተቋማት ንቁ ተሳትፎ እና አስተዋጽኦ ወሳኝነትን በመረዳት ውይይቱ መካሄዱን የገለጹት ምክትል ከንቲባዋ፣ የተደረገው ውይይትም ፍሬያማ መሆኑን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ መለሰ አለሙ የሀገር ግንባታን የማጠናከር ጉዳይ የሀሉም ዜጋ የዕለት ከዕለት ተግባር ሊሆን እንደሚገባና የሀይማኖት ተቋማት ድርሻም ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።

ምክትል ከንቲባዋ በመድረኩ ላይ ለተሳተፉ የእምነት ተቋማት፣ የሰላም ምክር ቤት አባላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ወጣቶች፣ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን አጠናክረው በመደማመጥ፣ በፍቅር፣ በአብሮነት እና በጋራ ኃላፊነት አዲስ አበባን በሰላም የምትታወቅ ከተማ ለማድረግ ተግተው ለመሥራት ቃል መግባታቸውን አመስግነዋል።

ህዝቡ ለሰላም ዘብ በመቆም በድህነት ላይ የጋራ ትግል ሊያደርግ እንደሚገባም የሀይማኖት አባቶች አሳስበዋል፡፡

በሀይማኖትና ብሄር ሳይለያይ የውጭ ጠላትን በመዋጋት ነፃነትን እንዳስጠበቀው ሁሉ ትውልዱ ለሰላም ዘብ በመቆም በድህነት ላይ የጋራ ትግል ሊያደርግ እንደሚገባ የሀይማኖት አባቶች መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸውን ከከተማዋ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።