የጁንታው አባላት በሀሰተኛ መታወቂያ ከሀገር ለመውጣት ያደረጉት ጥረት ከሽፏል -ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ

ሚያዝያ 15/2013 (ዋልታ) – የጁንታው አባላት ሀሰተኛ መታወቂያ በማዘጋጀት ከሀገር ለመውጣት ያደረጉትን ጥረት መከላከያ ሚኒስቴር ማክሾፉን በመከላከያ ሚኒስቴር የሰራዊት ግንባታ ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ ገለጹ፡፡
በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል እንዲሁም በአጣዬ የተነሱትን ግጭቶች አስመልክቶ ሀገሪቱን ለማፈራረስ የሚጥሩ አካላት ግጭቶቹ የብሄር እና የሐይማኖት መልክ እንዲኖራቸው መስራታቸውንም ጄነራሉ ገልጸዋል፡፡
መከላከያ ሚኒስቴር ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ዜጎችን እያወያየ እንደሚገኝ እና የተፈናቀሉ ሰዎችን መልሶ ለማቋቋም እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
በሀገሪቱ የሚታዩ ግጭቶችን ለመቅረፍ በዘጠኝ ወረዳዎችና አምስት ከተማ አስተዳደሮች የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት የማረጋጋት ስራ እየሰራ ስለመሆኑም ሌተናል ጄነራሉ ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል የሀገር መከላከያ ሚኒስቴርን ስም የማይመጥን የሀሰት ወሬዎችን በማናፈስ በሰራዊቱ ውስጥ መከፋፈል እንዲኖር የሚሰሩ አካላት መኖራቸውን የጠቀሱት ሌ/ጄነራል ባጫ ደበሌ፣ መከላከያ ሰራዊት ለህዝብ የቆመ በመሆኑ አይሳካላቸውም ብለዋል፡፡
(በመስከረም ቸርነት)