በዓለም ባንክ እና ኢትዮጰያ የ907 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ

ሚያዝያ 15/2013 (ዋልታ) – በዓለም ባንክ እና ኢትዮጰያ መንግስት የ907 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ እና የዓለም ባንክ ግሩፕ የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ሚኒስትር ኦስማን ዲዮን ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱ ሶስት ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ የሚውል ሲሆን፣ የመጀመሪያው የ200 ሚሊየን ዶላር ስምምነት በኢትዮጵያ ውስጥ በአነስተኛ እና ጥቃቅን ለተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች የሚውል ነው ተብሏል፡፡

የ500 ሚሊየን ዶላር ስምምነት በሀገሪቱ ውስጥ ለሚከናወኑ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እና ተደራሽነት ከማሳደግ ባሻገር የግሉ ዘርፍ ካፒታል ተሳትፎን እና ዘላቂ የፋይናንስ አማራጮችን ለማምጣት የሚያስችል አከባቢን ለመፍጠር መሆኑ ተገልጿል፡፡

ከዚህ ስምምነት 100 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ የሚውለው የግሉ ዘርፍ በኤሌክትሪክ አገልግሎት ሲሆን፣ የ207 ሚሊየን ዶላር ስምምነት የኮቪድ-19 ጉዳት ለመቀነስና ክትባቶችን ውጤታማ እና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲዳረስ ለማድረግ የሚውል መሆኑን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡

ስምምነቱን የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ፣ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ፍሬህይወት ወልደሃና፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው እና የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማስፋፊያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ ተፈራርመዋል፡፡