የካቲት 19/2014 (ዋልታ) የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በሀረሪ ክልል በጤናው ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ማጠናከር እንደሚገባ አሳሰቡ፡፡
ሚኒስትሯ ከሀረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሚስራ አብደላ ጋር በመሆን በክልሉ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማስተባበሪያ ማእከል እና የአውበርከሌ ጤና ኬላን ጎብኝተዋል።
ሚኒስትሯ ኅብረተሰቡን ከአደጋ ከመጠበቅ አንፃር እየተከናወኑ ያሉ አበረታች ተግባራት የበለጠ እንዲጠናከሩ ቅንጅታዊ ሥራን ማጎልበት ያስፈልጋል ማለታቸውን ከክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡
የሀረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሚስራ አብደላ በበኩላቸው ትክክለኛና የጠራ መረጃን በመያዝ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ከማድረግ አንፃር እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው ሚናቸውን በአግባቡ እየተወጡ ላሉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።