በኢትዮ- ሶማሊያ አዋሳኝ ድንበር አካባቢዎች የፀጥታ ሁኔታ ዙሪያ ውይይት ተደረገ

የካቲት 19/2014 (ዋልታ) በጁባላንድ ክልል የሰላም ሁኔታ እና በኢትዮጵያና ሶማሊያ አዋሳኝ ድንበር አካባቢዎች የፀጥታ ሁኔታ በተመለከተ ውይይት ተደረገ፡፡

ውይይቱን የመሩት የጁባላንድ ክልል ፕሬዝዳንት አሕመድ መዶቤ ኢትዮጵያና ሶማሊያ በታሪክ፣ ባህልና ቋንቋ የሚመሳሰሉ መሆናቸውን ጠቁመው ይህንን አንድነታችንን እና ወንድማማችነታችንን ለመሸርሸር አልሸባብ ሌት ተቀን እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

የሴክተር 3 አዛዥ ብርጋዴል ጄነራል ዘውዱ ሰጥአርጌ በሶማሊያ የጠላት ሽብርተኝነት፣ የጎሳ ግጭት፣ የፌዴራልና የክልል መንግሥት አለመግባባት ይሰተዋላል ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በሕዝቡ ዘንድ መረጋጋት እንዳይኖር የሚሰሩትን አካላት በጋራ ሆነን በመለየት የአገሪቱን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ ዝግጁ ነን ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የሴክተር 6 አዛዥ ብርጋዴል ጄነራል አበባው ሰይድ በበኩላቸው የአሸባሪ ቡድኑን ሴራ ለማክሸፍ ከመስተዳድር አካላት፣ ከፀጥታ ኃይሉና ከሕዝቡ ጋር በቅርበት በመገናኘት ችግሩን መፍታት ይገባል ብለዋል፡፡

በውይይቱ የጁባላንድ ክልል ፕሬዚዳንት፣ የሴክተር 3 አዛዥ፣ የሴክተር 6 አዛዥ፣ የ5ኛ ሞተራዝድ ዋና አዛዥና የጁባላንድ ክልል ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ እንዲሁም መረጃ ኃላፊ ተገኝተዋል፡፡