የፀጥታ ኃይሉ በአማራ ክልል የተሰባሰበውን ዘራፊና አጥፊ ቡድን በመምታት ከተሞቹ ወደ ሰላማዊ ሁኔታ እንዲመለሱ ተደርጓል – ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

ነሐሴ 5/2015 (አዲስ ዋልታ) የፀጥታ ኃይሉ በአማራ ክልል የተሰባሰበውን ዘራፊና አጥፊ ቡድን በመምታት ከተሞቹ ወደ ሰላማዊ ሁኔታ እንዲመለሱ ተደርጓል ሲሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ እስካሁን በተሰሩ ፀጥታ ሥራዎች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በአጠቃላይ ሁኔታዎች ላይ በሰጡት መግለጫ በባሕር ዳር፣ ደብረ ማርቀስ፣ ደብረ ብርሃን፣ ላሊበላ፣ ጎንደር እና ሸዋ ሮቢት አካባቢ የተሰባሰበውን ዘራፊና አጥፊ ቡድን በመምታት ከተሞቹ ወደ ሰላማዊ ሁኔታ እንዲመለሱ ተደርጓል ብለዋል፡፡

በከተሞቹ ውስጥና ዙሪያ የተሰገሰጉ ቡድኖች መሳሪያን እንዲያስረክብና እጁን ለፀጥታ ኃይሎች እንዲሰጥ የተሰጠውን ዕድል ባለመጠቀሙ አርምጃ እንደተወሰደባቸውም ገልጸዋል፡፡

የሕግ በላይነት እንዲከበር ተደርጓል ያሉት ሚኒስትሩ የአካባቢው ሕብረተሰብም በዘራፊው ቡድን ከመማረሩ የተነሳ የሕግ አስከባሪ አካላት ተልዕኳቸውን በስኬት እንዲወጡ የሚጠበቅበትን ድርሻ ሁሉ አበርክቷል ብለዋል፡፡

በዚህም ከተሞቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተሟላ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለሱ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

የየአካባቢዎቹ ማኅበረሰብም መረጃ በመስጠት፣ ከመከላከያ ሰራዊቱ ጋር በመሰለፍ፣ ስንቅ በማቀበል እንዲሁም የተዘጉ መንገዶችን በራሱ አቅም በመክፈት አቅሙ በፈቀደ ሁሉ ድጋፉን እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡